የግብፅ ግዙፉ የከፍተኛ ትምሕርት ተቋም አል አዝሃር ዩኒቨርሲቲ፣ እስራኤል የፍልስጤም እስረኞችን ለመግደል የሚያስችለውን የሞት ቅጣት ሕግ ማጽደቋን ተከትሎ ውሳኔውን በመቃወም መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫው እስራኤል የፍልስጤም እስረኞች ላይ የሞት ቅጣት ለመጣል ያሳለፈችው አዲስ ሕግ “ግድያን ሕጋዊ የማድረግ ሙከራ” ነው ሲል በጽኑ አውግዟል።
መግለጫው የመጣው የእስራኤል ፓርላማ ሕጉን በ62 ድጋፍ፣ በ48 ተቃውሞ እና በአንድ ድምፅ ተአቅቦ ካጸደቀ ከአንድ ቀን በኋላ ነው፡፡ የሕጉ መጽደቅ ተከትሎ በእስራኤል ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ዘንድ ደስታን ፈጥሮ ነበር፡፡ አልአዝሃር “የዓለም አቀፉ የሕግ ሥርዓት” የጽዮናውያን ወረራ በፍልስጤማውያን እስረኞች እና ታሳሪዎች ላይ የሞት ቅጣት ለመጣል ያሳለፈውን ረቂቅ ሕግ “ለመግታት አለመቻሉን እጅግ አሳዛኝ ነው” ብሎታል፡፡ አያይዞም የሕጉን መጽደቅ በጽኑ ኮንኖታል፡፡
ተቋሙ አክሎም ይህ ርምጃ “ባለማቋረጥ ከሚፈጽመው ወንጀል ያልተገታው ወራሪው ኃይል፣ አሁን ደግሞ ግድያን ሕጋዊ ለማድረግና የሐሰት የሕግ ሽፋን ለመስጠት መጣሩንና ደም አፍሳሽ ማንነቱን በድጋሚ ያጋለጠበት ነው” ብሏል። የፍልስጤማውያንን ግድያ ሕጋዊ ለማድረግ በማለም በወራሪው ኃይል የሚወጡ ማናቸውንም ውሳኔዎች እንደሚቃወም አፅንዖት ሰጥቷል። ውሳኔው “ለግድያ የሕግ ባሕርይ ለማላበስ የተደረገ ተስፋ ቢስ ሙከራ ቢሆንም የድርጊቱን እውነታ አይለውጠውም፤ ይልቁንም አረመኔነትን፣ የሥነ-ምግባር ውድቀትን እና ሁሉንም ሰብዓዊ እሴቶች መጣስን የሚያሳይ ነው” ሲል ገልጾታል።
አዲሱ የእስራኤል ሕግ በወረራ በተያዙ ግዛቶች በተለይም በዌስት ባንክ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በተለየ ሁኔታ ኢላማ ያደረገ ነው ተብሏል። በእስራኤል የሚገኘው የሲቪል መብቶች ማኅበር አዲሱን ሕግ በመቃወም ለእስራኤል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረቡን ገልጿል። የሕጉ መፅደቅ በተለያዩ ሀገሮች እና ድርጅቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞን ያስከተለ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሕጉ “ጭካኔ የተሞላበት እና የዘረኝነት መገለጫ” በማለት እስራኤል የሞት ቅጣትን በመጠቀም የአፓርታይድ ሥርዓቷን ለማጠናከር እየሠራች መሆኑን ገልጿል፡፡ ሕጉ ተከሳሾች በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እንዲዳኙ የሚያደርግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቶቹ ዓለም አቀፍ የፍትሕ መስፈርቶችን የማያሟሉ እና ለተከሳሾች ተገቢውን የጥበቃ መብት የማይሰጡ መሆናቸውን የጠቀስው አምነስቲ፤ የሕጉን መጽደቅ ነቅፏል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












