Homeዜናና ወቅታዊዜናበኢራን እና አሜሪካ ጦርነት ኪሳራውን ዐረብ ሀገሮች ሊከፍሉ ይሆን?

በኢራን እና አሜሪካ ጦርነት ኪሳራውን ዐረብ ሀገሮች ሊከፍሉ ይሆን?

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት 32ኛ ቀን ላይ ደርሷል፡፡ በጥቃቱ ኢራን ለአሜሪካና እስራኤል ጥቃት በሰጠችው ምላሽ የሆርሙዝን መተላለፊያ በመዝጋቷ፣ ከዓለም አቀፉ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ውስጥ አንድ አምስተኛውን አስተጓጉሏል። ይህ ሁኔታ ዓለምን ላለፉት ዐስርት ዓመታት ትልቁ ነው የተባለ የኢነርጂ ቀውስ ውስጥ ከቷታል።

አልጀዚራ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃንን ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው፣ ባለሥልጣናት ለኮንግረስ አባላት በሰጡት ምስጢራዊ መረጃ መሠረት የጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ቀናት ብቻ 11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናትና ምርምር ማዕከል ባወጣው ግምታዊ ሥሌት ደግሞ፤ ጦርነቱ በጀመረ በ12ኛው ቀን ወጪው ወደ 16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አሻቅቧል። ጦርነቱ አሁን 32ኛ ቀኑን በያዘበት ወቅት ደግሞ ወጪው ከዚህም እጅግ እንደሚያሻቅብ ይገመታል።

ይህ በእንዲህ ባለበት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ሰኞ ዕለት፣ “እ.ኤ.አ በ1990 በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ወቅት የአሜሪካ አጋሮች ለዋሽንግተን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረጉት ሁሉ፣ አሁንም የዐረብ ሀገሮች ለዚህ ጦርነት መክፈል አለባቸው ወይ?” የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸዋል፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ሌቪት፡ “በዚህ ጉዳይ ላይ ከፕሬዝዳንቱ [ትራምፕ] ቀድሜ መናገር ባልፈልግም ሐሳቡ አላቸው፤ ወደፊትም ከራሳቸው በሰፊው የምትሰሙት ይሆናል” ብለዋል፡፡ ጋዜጠኞቹ የጠቀሱት ጉዳይ የኢራቅ እና ኩዌትን ግጭት የተመለከተ ነው፡፡ በወቅቱ አሜሪካ “ኩዌትን ለመታደግ” በሚል በራሷ በኩዌት እና በጎረቤት ዐረብ ሀገሮች ጥያቄ መሠረት በርካታ ሀገሮችን ያቀፈ ዓለም አቀፍ ጥምረት መርታ ነበር። በምላሹ እንደ ጀርመን እና ጃፓን ያሉ የጥምረቱ አባላት እና የቀጣናው ሀገሮች አሜሪካ ለገባችበት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የሚውል 54 ቢሊዮን ዶላር አሰባስበው ነበር። የዐረብ ሀገሮች የ28 እድሜ ላላት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይዋ ካሮላይን ሌቪት ንግግር የሰጡት ምላሽ የለም፡፡

ይሁን እንጂ በዚህኛው ጦርነት አሜሪካ እና እስራኤል ሌሎች “አጋር” የሚሏቸውን ወይም የቀጣናውን ሀገሮች ሳያሳትፉ “በራሳቸው ውሳኔ” በኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ቅርብ የሆኑ የቀኝ ዘመም ተንታኞች የካሣ ጉዳይ ወደ ኢራን መገፋት አለበት የሚል ሐሳብ በሥፋት ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚጠቀሱት ሲን ሃኒቲ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሲናገሩ፤ “ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት ኢራን የጦርነቱን ወጪ እንድትሸፍን የሚያስገድድ መሆን አለበት” ብለዋል፡፡ ኢራን ለዚህ አጠቃላይ ወታደራዊ ዘመቻ የወጣውን ወጪ በሙሉ መክፈል ያለባት በዐይነት (ማለትም በነዳጅ) መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኢራን በአሜሪካ እና በእስራኤል ለተሰነዘሩባት ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት በመላው መካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ ኢላማዎች ላይ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶችን ሰንዝራለች። ዋይት ሐውስ በበኩሉ በኢራን ላይ የሚካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ ለመደገፍ እና የፔንታጎን የጦር መሣሪያ ክምችቶችን ለመተካት ቢያንስ 200 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወታደራዊ በጀት ከኮንግረስ እየጠየቀ ይገኛል።

ጦርነቱ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ጎን ለጎን በፓኪስታን ዋና አደራዳሪነት የሽምግልና ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ በዚህም የሳዑዲ ዐረቢያ፣ የቱርክ እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ቅዳሜ እና እሑድ ፓኪስታን ኢስላማባድ ተጉዘው ነበር፡፡ ይህ በሁለት ሣምንት ውስጥ የተካሄደ ሁለተኛው ዲፕሎማሲ ስብሰባ ነበር። በኢስላምአባድ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ የፓኪስታኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢስሓቅ ዳር፣ የቱርክ አቻቸው ሐካን ፊደን፣ የግብጹ በድር ዓብዱልዓጢ እና የሳዑዲ ዐረቢያው ልዑል ፈይሰል ቢን ፈርሐን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ አሜሪካ እና ኢራን በመካከላቸው የሚደረገውን ቀጥታ ንግግር ሀገራቸው እንድታመቻች “ሙሉ እምነት” እንዳላቸው ገልጸዋል። በቀጣዮቹ ቀናት፣ ለቀጠለው ግጭት “አጠቃላይ እና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት” ኢስላምአባድ ትሠራለች ብለዋል፡፡ ኢስሓቅ ይህን ቢሉም የነዳጅ ዋጋ አሻቅቦ የሀገሮችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማስተጓጎሉን እንደቀጠለ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular