አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ ዛሬ ጁምዐ 28ኛ ቀን ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ ሣምንት ግን “ጦርነቱ ጋብ ሊል ይሆን ወይ?” የሚያስብለው መረጃ ወጥቷል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ድርድር ስለማድረግ ሲናገሩ፤ በአስታራቂነት የተጠራችው ፓኪስታን ነች፡፡ ቱርክ እና ግብጽም በሽምግልናው ተሳታፊ ናቸው፡፡ የኢራን ባለሥልጣናት ለአስታራቂዎች እንደገለጹት፤ አሁንም ከሀገሪቱ “ከፍተኛ አመራር” የይለፍ ፍቃድ እየጠበቁ ስለሚገኙ “መልስ መስጠት አይችሉም”፡፡
ይህ በእንዲህ ባለበት አሜሪካ ተደራዳሪዋን ሠይማለች፡፡ ሀገሪቱን የሚወክሉት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እንደሚሆኑ ይፋ ተደርጓል፡፡ ድርድሩ ተሳክቶ የሚካሄድ ከሆነ፤ ቫንስ ከኢራን የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሙሐመድ ባገር ጋሊባፍ ጋር ፊት ለፊት ይገናኛሉ [የኢራን ከፍተኛ መሪ መገደላቸውን ተከትሎ፣ ጋሊባፍ በድርድሩ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ግለሰብ ናቸው]፡፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትናንት ሐሙስ በተካሄደው የካቢኔ ስብሰባ ላይ የቫንስን ሚና ይፋዊ አድርገዋል። በዚሁ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንቱ ስለ ኢራን ጉዳይ አዳዲስ መረጃዎችን እንዲያቀርቡ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ጋብዘው፤ ቫንስም በድርድሩ ሂደት ውስጥ ከስቲቭ ዊትኮፍ እና ከጃሬድ ኩሽነር ጋር አብረው እየሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

አክሲዮስ የአሜሪካ እና እስራኤል ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ፤ ቫንስ እስራኤልን ቢደግፉም ጦርነቱ እንዴት ሊካሄድ እንደሚችል የእስራኤል ባለሥልጣናት ጥቃት ከመክፈታቸው በፊት የነበራቸው “እጅግ አዎንታዊ ግምገማ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ” ነበራቸው፡፡ በዚህ ሰበብ አሁንም ቢሆን ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር መግባባት አልቻሉም፡፡ የቫንስ አማካሪዎች በእስራኤል ውስጥ ያሉ አንዳንዶች በጦርነቱ “[ቫንስ] መራር መሆን ተስኗቸዋል” (በራሳቸው አገላለጽ hawkish አይደሉም) በሚል ምክንያት ሥራቸውን ለማደናቀፍ እየሞከሩ ነው ብለው ያምናሉ። የእስራኤል ባለሥልጣናት ይህን ክደዋል፡፡
የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት ግን የእስራኤል ሰዎች በቫንስ ላይ ሥም ማጥፋት ለማካሄድ እየሞከሩ እንደሆነ መጠራጠር የጀመሩት ባለፈው ሰኞ በኔታንያሁ እና በቫንስ መካከል የተደረገውን “አስቸጋሪ” የተባለ የስልክ ውይይት ተከትሎ ነው። በዚሁ የስልክ ጥሪ ወቅት ቫንስ ኔታንያሁ ስለ ጦርነቱ ቀደም ብለው የተነበዩዋቸው በርካታ ነገሮች “ከልክ በላይ የተለጠጡ” እንደነበሩ አንስተዋል፡፡ በተለይም የኢራንን ሥርዓት ለመጣል ሕዝባዊ አመፅ ይነሳል በሚል ያስቀመጡት ግምት ስህተት መሆኑን ነግረዋቸዋል፡፡
አንድ የአሜሪካ ምንጭ ሲናገሩ:- “ከጦርነቱ በፊት ኔታንያሁ ለፕሬዝዳንቱ ነገሩን በጣም ቀላል አድርገው አቅርበውት ነበር፤ የሥርዓት ለውጥ የመምጣቱ ዕድልም ካለው በላይ ከፍተኛ እንደሆነ አድርገው ነበር ለአሜሪካ ‘የሸጡት’፤ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ግን ይህን ሲሉ ተላላ አልነበሩም” ብለዋል፡፡

ቫንስ ረቡዕ ዕለት ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑካን ቡድን ጋር፣ ትናንት ሐሙስ ዕለት ደግሞ ዋሺንግተን ከሚገኙት ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው መክረዋል። ሁለቱም ስብሰባዎች ትኩረታቸውን ያደረጉት በጦርነቱ፣ ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር እና ለሁለቱ የባህረ ሰላጤው አጋሮች በሚሰጠው ወታደራዊ ርዳታ ላይ ነበር።
አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን እንደገለጹት፣ ቫንስ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊትም ሆነ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከኢራን ጋር በሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ በሰፊው ተሳትፈዋል፡፡ በኢራን ከተነሳው ተቃውሞ አንስቶም ጦርነቱ እስከፈነዳበት ጊዜ ድረስ፣ በኢራን ላይ ስለሚወሰዱ ወታደራዊ አማራጮች የሚመክሩ በርካታ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ስብሰባዎችን በሊቀመንበርነት የመሩት እርሳቸው ናቸው፡፡ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ሲናገሩ፤ “ኢራናውያን ከቫንስ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ፣ ከሌሎች ጋር ስምምነት መድረስ ይቸግራቸዋል። ለእነርሱ [ለኢራናውያን] ምርጡ ሰው እሱ ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ ባለሥልጣኑ ምክትል ፕሬዝዳንቱ የራሳቸው አመለካከት ቢኖራቸውም፣ “በትራምፕ መመሪያ መሠረት እንደሚሠሩ” አያይዘው መናገር አልዘነጉም፡፡ የኢራን ባለሥልጣናት ግን አሁንም ቫንስን ለማግኘት “አረንጓዴው መብራት እስኪበራ” እየጠበቁ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












