የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነባውን የንጉሥ ነጃሺ እስላማዊ ማዕከል የግንባታ ሒደት እንዲሠሩ ሚድሮክ ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ለሀገር ውስጥ ባለሐብቶች አስረክቧል፡፡ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 17/2018 በተከናወነ ሥነ ሥርዐት ይህን ይፋ አድርጓል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ግንባታውን ለሀገር ውስጥ ባለሐብቶች ማስተላለፉን ያስታወቀው፤ የማዕከሉ ግንባታ ከውጭ ባለሐብቶች እጅ ወጥቶ በኢትዮጵያውያን እንዲገነባ ውሳኔ ማሳለፉን ከገለጸ ከሦስት ሣምንት በኋላ ነው። ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ይህንን የተናገሩት የካቲት 28/2018 በአዲስ አበባ አብዮት አደባባይ በተከናወነው የጎዳና ላይ ኢፍጣር ወቅት ነበር፡፡
በዛሬው ሥነ ሥርዐት ላይ በሒደቱ በሚድሮክ ዋና አስተባባሪነት አራት ኢትዮጵያውያን ባለሐብቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል። በጠቅላይ ምክር ቤቱ የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የማዕከሉ ግንባታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ እስከዛሬ የነበረው ሂደት ላይ ገልጻ በማድረግ ከዚህ በኋላ የሚኖረውን ኃላፊነት ለባለሐብቶች አስረክበዋል፡፡

በዲዛይን ርክክብ ሥነ ሥርዐቱ ላይ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አሕመድ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ባለቤት ሸይኽ ሙሐመድ ዓሊ አል አሙዲ ፕሮጀክቱን በመረከባቸው “በጣም የተደሰቱበት ቀን” ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ፤ የማዕከሉን ግንባታ በተመለከተ አሁንም ከተለያዩ የውጭ አካላት ጥያቄ ቢቀርብም ለሀገር ውስጥ ባለሐብቶች መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
ለሀገር ውስጥ ባለሐብቶች የተላለፈው የንጉሥ ነጃሺ እስላማዊ ማዕከል፤ በሚያዝያ 2012 በመንግሥት በተሰጠ 30 ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ የማዕከል ግንባታው ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ይፋ ያደረገው የባለሞያ የመጀመሪያ ደረጃ ግምት ያመለክታል፡፡ የማዕከሉን ግንባታ የበጀት ምንጭ በተመለከተ ከዚህ ቀደም በሳዑዲ ዐረቢያ መቀመጫውን ያደረገው ዘ ሙስሊም ወርልድ ሊግ በዋና ጸሐፊው ዶክተር ሙሐመድ ዓብዱልከሪም ዒሳ በኩል ቃል ቢገባም ተግባራዊ ሳያደርግ ቆይቷል፡፡
ማዕከሉ ሲጠናቀቅ መስጂድን ጨምሮ የንግድ መደብሮችን ያካትታል ተብሏል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












