ኢራን የሆርሙዝ ስትራተጂካዊ የባሕር ዳርቻን በመቆጣጠር የምግብ ዋስትና ሥጋት እየጨመረ በመምጣቱ፤ ፓኪስታን ተጨማሪ የምግብ አቅርቦቶችን ወደ ባሕረ ሰላጤ ሀገሮች መላክ እንደምትጀምር አስታውቃለች፡፡
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሸሪፍ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ሀገሪቱ ያልተቋረጠ አቅርቦትን በማረጋገጥ ትርፍ ምርቶች በአፋጣኝ ወደ ባሕረ ሰላጤው ሀገሮች እንዲላኩ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡ ኢስላማባድ፤ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ምክንያት የበረራ አገልግሎትን ለማስፋት እና የወደብ አቅምን ለማሳደግ እንደምትፈልግም መግለጫው ያመለክታል፡፡
ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ ኢራን ሆርሙዝን ተቆጣጥራ የራሷን ኮሪደር ሥርዓት እየዘረጋች ነው። በውሃ መንገዱ ያለው ትራፊክ ቢቋረጥም ሀገሪቱ የተወሰኑ መርከቦችን እንዲዘዋወሩ ትፈቅዳለች፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች ሁለት ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እንደምትቆርጥም የሎይድ ሊስት የባሕር ውስጥ መረጃ አመልክቷል፡፡
በኢራን እና በኦማን መካከል የሚገኘው ሆርሙዝ የምድራችንን አንድ አምስተኛው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ከማስተላለፍ ባሻገር ለባሕረ ሰላጤው ሀገሮች የምግብ አቅርቦት ወሳኝ መሻገሪያ ነው።
ወደ ቀይ ባሕር መዳረሻ ያላቸው እንደ ሳዑዲ ዐረቢያ ያሉ ሀገሮች በመተላለፊያው መዘጋት እምብዛም ባይጎዱም፤ ለዩናይትድ ዐረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌት፣ ባሕሬን እና ኳታር ግን ወሳኝ ነው። የዩናይትድ ዐረብ ኤምሬትስ 90 በመቶ ገደማ የምግብ አቅርቦት የሚተላለፈው በውሃ መስመሩ በኩል ነው። ባለሞያዎች ቀደም ሲል የሆርሙዝ ጠረፍ ለመርከቦች ዝግ ሆኖ ከቀጠለ የምግብ እጥረት ሊገጥም እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ ነበር፡፡
አሁን ለሀገሮቹ የምግብ ምርት እንደምትልክ ያሳወቀችው ፓኪስታን፤ በሆርሙዝ ጠረፍ ላይ በሰላም መጓዝ ከተፈቀደላቸው ጥቂት ሀገሮች አንዷ ነች። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ፣ “ካራቺ” በመባል የሚጠራ የፓኪስታንን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልብ መርከብ በሆርሙዝ አቋርጧል። ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው፤ ኢራን ለዓለም አቀፍ የባሕር ድርጅት አባል ሀገሮች በጻፈችው ደብዳቤ፤ “ጠላት ያልሆኑ መርከቦች” ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር የሆርሙዝ ጠረፍን ማቋረጥ ይችላሉ ብላለች፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












