Homeዜናና ወቅታዊዜናከኢትዮጵያ በምሥራቃዊ መስመር በኩል የሚወጡ ፍልሠተኞች ቁጥር በ18 በመቶ ጨምሯል - አዲስ...

ከኢትዮጵያ በምሥራቃዊ መስመር በኩል የሚወጡ ፍልሠተኞች ቁጥር በ18 በመቶ ጨምሯል – አዲስ ሪፖርት

ዓለም አቀፍ የፍልሠተኞች ድርጅት፤ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ከኢትዮጵያ በምሥራቃዊ መስመር በኩል የሚወጡ ፍልሠተኞች ቁጥር በ18 በመቶ መጨመሩን አዲስ ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ “አደገኛ ነው” በሚባለው በዚህ መስመር የተመዘገበው አጠቃላይ የፍልሠተኞች እንቅስቃሴ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ18 በመቶ በመሻቀብ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መድረሱም ተገልጿል፡፡

የምሥራቃዊ መስመር በዓለም ላይ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ፍልሠተኞች የሚተላለፉበትና እንቅስቃሴ ከሚበዛባቸው መስመሮች አንደኛው ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ፍልሠተኞች መደበኛ ባልሆነ መንገድ በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ይጓጓዛሉ፡፡ በዚህ መስመር በ2024 የተመዘገበው 430 ሺሕ 200 የሰዎች ቁጥር፤ በ2025 ወደ 506 ሺሕ 600 ከፍ ብሏል፡፡

ሪፖርቱ ለዚህ ቁጥር ማሻቀብ በምክንያት ያስቀመጠው አዘዋዋሪዎች የፍተሻ ጣቢያዎችን ለማለፍ የሚጠቀሙባቸውን ሥልቶች መለዋወጣቸውና በጅቡቲ በኩል ያሉ አማራጭ መንገዶችን ነው፡፡ በመስመሩ ከሚጓዙ ፍልሠተኞች መካከል 97 በመቶ ገደማ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ 95 በመቶው ለስደት የዳረጋቸው ዋነኛ ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር መሆኑ ተገልጿል፡፡ መነሻቸው በአብዛኛው ከአማራ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ አካባቢዎች ነው፡፡ ፍልሠተኞቹ ጎረቤት ሶማሊያ እና ጅቡቲን በመተላለፊያነት ይጠቀማሉ።

በዚህ መስመር የሰዎች እንቅስቃሴ የክትትል ሥራ ከተጀመረበት ከ2014 ወዲህ የቀደመው ዓመት እጅግ አስከፊው ዓመት ሆኖ አልፏል። በዓመቱ 922 ፍልሰተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል አልያም ደብዛቸው ጠፍቷል፡፡ ይህም በ2024 ከነበረው 558 የሟቾች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ገደማ ብልጫ ተመዝግቦበታል፡፡

በሪፖርቱ የተጠቀሰው ሌላኛው ጉዳይ ከሳዑዲ ዐረቢያ በግዳጅ የሚመለሱ ፍልሠተኞች ቁጥርም ጭማሪ ማሳየቱ ነው። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 95 ሺሕ 100 ፍልሠተኞች ሲመለሱ፤ በአጠቃላይ እ.ኤ.አ ከ2017 ጀምሮ የተመላሾችን ቁጥር ከ750 ሺሕ በላይ አድርሶታል። በግዳጅ የሚመለሱ ሕፃናት ቁጥርም በ14 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡ ለዚህ ምክንያት ተደርጎ የተቀመጠው ሴት ተመላሾች ሳዑዲ ወልደው ወደ ሀገር ቤት መምጣታቸው ነው፡፡

ፍልሠተኞች በታጠቁ ኃይሎች የሚፈጸምባቸው ጥቃት፤ እስራት፣ የጎርፍ አደጋ፣ እንግልት እና ከአዘዋዋሪዎች የሚደርስባቸው በደል ጉዟቸውን አስከፊ እንደሚያደርገው ተጠቅሷል። ድርጅቱ አክሎም፣ በ2026 በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይታያል ተብሎ የሚጠበቀው የኢኮኖሚ እድገት የፍልሠት ጫናውን ሊቀንሰው ቢችልም፤ “የኑሮ ውድነት እና የሥራ አጥነት ችግር” አሁንም ለመቀጠሉ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular