Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችአልጀዚራ ሠላሳ ደፈነ

አልጀዚራ ሠላሳ ደፈነ

ከሠላሳ 30 ዓመት በፊት ነው፤ አሕመድ አል ሸይኽ የቢቢሲ ዐረቢኛ ጋዜጠኛ ሆኖ ይሠራ ነበር፡፡ በድንገት ግን ቢቢሲ የዐረቢኛ ቴሌቪዥን አገልግሎቱን መዝጋቱን አስታወቀ፡፡ ይህ ውሳኔ የመጣው አገልግሎቱ አየር ላይ ከዋለ ገና ሁለት ዓመት እንኳ ሳይሞላው ነበር። ይህን ጊዜ አዲስ ሥራ መፈለግ ግድ ሆነበት፡፡ አንድ የሥራ ባልደረባው በለንደን የሚገኝ ቡድን በኳታር ሊጀምር ላሰበው የቴሌቪዥን የዜና ጣቢያ ጋዜጠኞችን እየመለመለ ነው የሚል ወሬ ይዞ መጣ። ጣቢያው ልክ በምዕራቡ ዓለም ያሉ ታዋቂ የዜና አውታሮች እንደሚያደርጉት፣ ዜናዎችን የመዘገብ እና የውይይት ፕሮግራሞችን እንደ አስፈላጊነታቸው “በነጻነት የማስተላለፍ መብት ይኖረዋል” አለው፡፡

በባልደረባው ጥያቄ ድንግርግር ያለው አሕመድ፤ “ምንድን ነው የምታወራው፣ ለመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ ነገር በዐረብ ሀገር ውስጥ በርግጥ ሊታሰብ የሚችል ነው?” የሚል ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ በጊዜው አጥጋቢ መልስ ባያገኝም ወደ ዶሐ አለመብረር አልቻለም፡፡

መዲናዋ ሲደርሱ ያገኙት የዜና ክፍል ጠባብ ነበረች። ከጎኗም እንዲሁ አነስተኛ ስቱዲዮ፣ ከጀርባቸው ደግሞ አምስት ትናንሽ የቪዲዮ ማቀናበሪያ (ኤዲቲንግ) ክፍሎች፣ የቪዲዮ ካሴት መዝገብ ቤት፣ የዋና አዘጋጁ ቢሮ እንዲሁም የዋና ዳይሬክተርና የሠራተኞቹ ቢሮ የያዘው ሰፊው ቤት ይገኝ ነበር።

አሕመድ በጥርጣሬ ባመራበት አዲስ ጣቢያ ሥራ በመጀመር ለአምስት ወራት በቆየው የሙከራ ሥርጭት ወቅት፣ ቡድኑ በየቀኑ በጥንካሬና በአንድነት እያደገ ሲሄድ ተመልክቷል፡፡  

ይሁን እንጂ ሁሉም ባልደረቦች “የተገባው የነጻነት ቃል ኪዳን በተግባር እውን ይሆን ወይ ብለን መጠራጠራችን አልቀረም” ይላል፡፡ አስከትሎም፣ እያንዳንዱን የዜና እትም ባጠናቀቅን ቁጥር ግን ያ ጥርጣሬ ቀስ በቀስ እየጠፋ ሄደ። በይዘቱ፣ በዘገባዎቹ ወይም ታሪኮቹ በሚቀርቡበት መንገድ ላይ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አላየንም። ብዙም ሳይቆይ፣ የተሰማን ቅሬታ ሌላ ዓይነት ሆነ። ከቢቢሲ ጋር የሚወዳደሩ፣ አልፎ ተርፎም የሚበልጡ የዜና እትሞችን እያዘጋጀን ነበር፣ ነገር ግን ተመልካች ሊያያቸው አይችልም ነበር።

እ.አ.አ ኖቬምበር 1/1996 ግን የእነ አሕመድ ቁጭት ምላሽ አገኘ፤ የዐረቡ ዓለምም በመጨረሻ የራሱን ድምፅ አገኘ። በአልጀዚራ የመጀመሪያ የዜና ሥርጭት ላይ ጀማል ረያን የጣቢያውን መጀመር ለዓለም አወጀ። ከዚህ በኋላ የሆነው ታሪክ ነው፤ አልጀዚራ ተናግሮ የሚደመጥ ድምጽ፣ ተከታይ ሳይሆን የሚያስከትል – “ምን አለ?” የሚባል ጣቢያ መሆኑን ዓለም ታዝቧል፡፡

ይህ ታሪክ ትናንት እሑድ ሠላሳ ዓመት ደፈነ፡፡ ሦስት ዐስርት ዓመታት ቆይታውን በተመለከተ የተናገሩት የአልጀዚራ ዳይሬክተር ሸይኽ ናስር ቢን ፈይሰል አስሣኒ፤ የኳታር አባት የሚባሉት ሸይኽ ሐማድ ቢን ኸሊፋ አስሣኒ ጣቢያው ሥራ ሲጀምር ቃል የገቡት፤ አንድን ርእሰ ጉዳይ ወይም ዜና ሲዘግቡ የአንዱን ወገን ሐሳብ ብቻ ሳይሆን የሌላኛውንም ወገን ዕይታ፣ መረጃ እና እኩል ማቅረብን የሚያሳየውን “አረዕይ ወረዕይ አል አኸር” የሚለው መፈክር የይስሙላ ሳይሆን እውን መሆኑ በጽናት የተረጋገጠበት ጉዞ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ጣቢያው ሠላሣ ዓመት ሲደፍን፣ ከዲጂታል ይዘቱ በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት ከ430 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተደራሽ መሆን ችሏል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ተቋሙ እሑድ እለት ከጉግል ክላውድ ጋር በመተባበር “ዘ ኮር” የተሰኘ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) ኢኒሼቲቭ ይፋ አድርጓል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ይፋ የተደረገው ይህ ፕሮጀክት፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በዜና ክፍል አሠራር ውስጥ በማዋሐድ ጋዜጠኞች መረጃዎችን እንዲያደራጁ፣ የዜና ሽፋን ሥራዎችን እንዲያቀናጁ እና የተቋሙን “አርካይቭ” ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ለማገዝ ያለመ ነው፡፡

ጣቢያው ሠላሳ ዓመት ሲደፍን ጉዞው ከትችት የጸዳ አልነበረም፡፡ በአንዳንድ ተቺዎቹ በኳታር መንግሥት የገንዘብ ድጎማ ስለሚንቀስቀስ በፖለቲካ ወገንተኝነት ክስ ይቀርብበታል፣ የኦሳማ ቢን ላደንን ቃል መጠይቅ በማስረጃ ቀርቦም በአሜሪካ “የጽንፈኛ መድረክ” በሚል ይወነጀላል፣ በዐረብ ጸደይ ወቅት ሕዝባዊ እምቢተኝነትን በማቀጣጠል ሀገራት እንዳይረጋጉ በማድረግም ተከሷል፡፡ በዐረቢኛ እና እንግሊዝኛ ቻነሎች የይዘት ልዩነት ያደርጋል “ሁለት ዐይነት መልክ አለው” በሚል የሚነቅፉትም አሉ፤ እነዚህ ተቺዎች ዐረቢኛው ይበልጥ ወግ አጥባቂ እና ሕዝበኛ እንዲሁም እንግሊዝኛው ደግሞ ለምዕራባዊያን እድምተኞች ተስማሚ፣ ለነጻነት እና “ሊበራል” አስተሳሰቦች ትኩረት የሚሰጥ ሆኖ ቀርቧል በሚል ሐሜት ይቀርብበታል፡፡ ተቺዎቹ ይህን ቢሉም ጣቢያው “የግፉዓን ድምጽ” ተደርጎ መታየት እንደሚፈልግ ኃላፊዎቹ ይበልጥ አጉልተው ለማሳየት ሲጥሩ ደጋግመው ታይተዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular