በዛሬው እለት እየተካሄደ የሚገኘው በአሜሪካ የሕግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በሙስሊሞች ላይ የሚሰነዘረው ጥላቻ እና መድልዖ ጨምሮ በመታየቱ፣ ከግዛቶች መካከል በቴክሳስ ግዛት የሚኖሩ አሜሪካውያን ሙስሊሞች መብታቸውን ለማስከበር እና ድምጻቸውን ለማሰማት ወደ ምርጫ ኮሮጆ ያመራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጥላቻው ይበልጥ አይሎ ታይቷል የተባለው በሚቺጋን ሴኔት ተወዳዳሪው ዓብዱረሕማን ሙሐመድ – ዓብዱልሰይድ ባሉ ዲሞክራት እጩዎች ላይ ነው፡፡ በቴክሳስ ግዛት ሙስሊም እጩዎች ባይኖሩም የዘንድሮው ምርጫ ውጤት ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ነዋሪዎች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ አልጀዚራ ያናገረው በሂዩስተን የእስልምና ማዕከል የተገኘው የ45 ዓመቱ ጠበቃ ሰሚር ነድጃ፤ “ችግሩን ይበልጥ የምንረዳው በልጆቻችን በኩል ነው፣ በትምህርት ቤት ልጆቻችን ከአንዳንድ ቤተሰቦች በሚወጡ አሳዛኝ አስተያየቶች ይበሳጫሉ” ብለዋል፡፡
በዚህም ምክንያት በቴክሳስ ሕዝብ ቁጥር ከ2 በመቶ ያነሰ ድርሻ ያላቸው ሙስሊሞች፣ የተደራጀ የምርጫ ተሳትፎ በማድረግ የፖለቲካ ተጽዕኗቸውን ለማሳየት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በርካታ መስጂዶችን በስሩ የሚያስተዳድረው ኢስላሚክ ሶሳይቲ ኦፍ ግሬተር ሂዩስተን ፕሬዝዳንት ኢምራን ጋዚ እንደገለጹት፣ ማኀበሩ የምርጫ ምዝገባ ቅስቀሳውን በማስፋት የእስልምና መሪዎችም በጁመዓ ሰላት ወቅት ሕዝቡ በነጻነት ድምጹን እንዲሰጥ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ጋዚ አክለውም “ፖለቲከኞች ሙስሊሞች ላይ ማንኛውንም ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው እንዲረዱ እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል እንደ ቴክሳስ ገዥ ግሬት አቦት እና ሴናተር ቴድ ክሩዝ ያሉ የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪዎች በእስልምና ሕግ (ሸሪዓ) ሥም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በቴክሳስ ላይ አደጋ ደቅነዋል በሚል ጥብቅ አቋም ይዘዋል፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የፓርቲው ኮንቬንሽን ላይ የቴክሳስ ሪፐብሊካን ፓርቲ “በቴክሳስ ምድር የሸሪዓ ሕግ አይሠራም” የሚል መመርያ የጸደቀ ሲሆን፣ በቴክሳስ ምክር ቤት ውስጥ የተቋቋመው “ከሸሪዓ ነጻ የሆነ የቴክሳስ ኮከስ” የተሰኘ 38 አባላትን አፍርቷል፡፡ ይህ ዘመቻ የሙስሊሞች መብቶች ተሟጋቾች እና የአካባቢው ነዋሪዎችን ክሶቹን ተከላካይ አድርጓቸዋል፡፡ በመከራከሪያቸው ቴክሳስም ሆነ በአሜሪካ የትኛውም አካባቢ የሸሪዓ ሕግ አልተተገበረም የሚሉት ነዋሪዎች፣ ፖለቲከኞች የማኅበረሰቡን ተራ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ እና ሕጋዊ ስብሰባዎችን እንደ ሥጋት አድርገው ማቅረባቸውን ይቃወማሉ፡፡
በአሜሪካ ትልቁ የሙስሊሞች መብት ተሟጋች ቡድን ‘ካውንስል ኦን አሜሪካ ኢስላሚክ ሪሌሽንስ’ ተወካይ ሰሚሀ ሪዝቪ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታየውን “ነገሮችን ዝም ብሎ የሚቀበል” አመለካከት በመቃወም፣ መብታችንን ለማስከበር እና ለቤተሰቦቻችን ደኅንነቷ የተጠበቀ ግዛት ለመፍጠር ያለው አጭሩ መንገድ ድምጻችንን በምርጫ መስጠት ብቻ ነው” ስትል ማኅበረሰቡ ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዲሄድ ጥሪ አቅርባለች፡፡ የመብቶች ተሟጋቹ ቡድኑ ባለፈው ሣምንት ባካሄደው የዳሰሳ ጥናትም በሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ የመምረጥ ፍላጎት ታይቷል፡፡
በዛሬው እለት እየተካሄደ የሚገኘው ምርጫ በተለይም በፖስታ በተላኩ ድምጾች እስከ ምርጫው ቀን እና ከዚያ በኋላ ባሉ ቀናት መቆጠር በሚችሉባቸው እንደ ካሊፎርንያ ባሉ ግዛቶች ምክንያት የሕዝብ ተወካዮች እና የሴኔት ምክር ቤት አብላጫ ድምጽ የማን እንደሚሆን ለማወቅ ጥቂት ቀናት ይወስዳል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












