Homeዜናና ወቅታዊዜናብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን መጠቀም...

ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን መጠቀም ሊቀጥል ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በስምንተኛ ስብሰባው ላይ የቀረቡ ሦስት የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ላይ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡ ኮሚቴው ይህን ውሳኔ ያሳለፈው ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 24፤ 2019 ባካሄደው ስብሰባ ነው፡፡ ባንኩ “እየታየ ባለው መጠነኛ ልቅ የገንዘብና ፋይናንስ ሁኔታ” የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ ባለበት 16 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል ወስኗል፡፡

ማዕከላዊ ባንኩ ባሰራጨው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው ያስፈለገው “እየታየ ባለው መጠነኛ ልቅ የፋይናንስ ሁኔታ” እና “በባለ ሁለት አሐዝ ይቆያል ተብሎ የተነበየውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር” ነው፡፡ የገንዘብ ፖሊሲውን ለማስጠበቅም “ሁሉንም ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን” እንደሚጠቀም ያመለከተው ባንኩ፤ በተለይም በኢኮኖሚው ውስጥ “ከሚጠበቀው በላይ ትርፍ ገንዘብ ሲኖር” ከባንኮች ጋር የሚያደርገውን የጨረታ ሰነድ ግብይት እንደሚጠቀም ጠቁሟል፡፡

የወደፊት የዋጋ ግሽበት አዝማሚያን በተመለከተ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት እየቀነሰ ይሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም የሚቆየው ግን በድርብ አሐዝ ውስጥ እንደሚሆን ትንበያ አስቀምጧል። 

በባንኩ መረጃ መሠረት፤ የምግብ ዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር 2018 ከተመዘገበው 15.1 በመቶ ወደ 14.8 በመቶ በመጠኑ የቀነሰ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ደግሞ ከ12.2 በመቶ ወደ 15.1 በመቶ ከፍ ማለቱን አስታውቋል። ለዚህ ምክንያት ነው ያለው በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ሳቢያ አቅርቦት በመስተጓጎሉ ነው፡፡

በምግብ ዋጋ ግሽበት ረገድ፣ የዳቦና የእህል ምርቶች፣ የአትክልትና ጥራጥሬ ምርቶች፣ እንዲሁም የቡና ዋጋ መጨመር ለዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በመግለጽ፤ ለምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች ጭማሪ ደግሞ በተለይም የኤሌክትሪክ ታሪፍ፣ የኬሮሲን እና የማገዶ እንጨት ዋጋ መጨመር ምክንያት እንደሆኑ አስቀምጧል።

የብድር ዕድገት ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ ተነስቶ ባንኮች ከፍተኛ ቁጠባ ቢሰበስቡም፤ የሰጡት አዲስ ብድር ከአጠቃላይ ተቀማጭ እና ተመላሽ ሲነጻጸር እድገት አለማሳየቱን እንዲሁም ከባለፈው ሩብ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ተቀራራቢ መሆኑን ገልጿል።

የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነዶች አማካይ የወለድ ምጣኔ እና ባንኮች እርስ በእርስ የሚበዳደሩበት የ7 ቀን የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ አማካይ የወለድ ተመኖች ከግንቦት ወር 2018 ጀምሮ ማሽቆልቆል ማሳየቱንም አክሏል። ለዚህም ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው ዋነኛው ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ያላቸው ትርፍ ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

ብሔራዊ ባንኩ እየተገበረዉ የሚገኘው መደበኛ የባንኮች የመጠባበቂያ ተቀማጭ እንዳለ ሆኖ፤ የብድር ዕድገት መስፋፋት በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር ሆኖ ሲገኝ፣ በሚያካሂደው መደበኛ ግምገማ መሠረት የእያንዳንዱን ባንክ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ ጥመርታ ላይ በመመርኮዝ የተለየ የመጠባበቂያ ተቀማጭ መተግበሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular