የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር፤ ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ከ2019 ጀምሮ መለካት የሚያስችለውን አዲስ ሥሌት ይፋ አድርጓል። ሚኒስቴሩ መለኪያውን ይፋ ያደርገው ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 25/2019 ነው፡፡
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው፤ ኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ወቅታዊ ስታደርግ 2017 በጀት ዓመት ቋሚ መነሻ ዓመት ተደርጎ ተመርጧል፡፡ ሚኒስቴሩ ይህን ለማድረጉ፤ የተመረጠው ዓመት አንፃራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት የታየበት፣ የዋጋ ግሽበት ምጣኔ እየቀነሰ የነበረበት፣ ከምርጫ ዓመት ውጪ በመሆኑ፣ የግብርና ቆጠራና የኢኮኖሚ ተቋማት ቆጠራ የተደረገበት ዓመት እንዲሁም የቤተሰብ ፍጆታ ጥናት የተሠራበት መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1960 ጀምሮ የጠቅላላ ሀገራዊ ምርት መረጃዋን በይፋ ስታሳውቅ ቆይታለች ያለው ሚኒስቴሩ፤ ሆኖም እስካሁን ሥራ ላይ የነበረው የ2008 የመነሻ ዓመት ስሌት በኢኮኖሚው የተፈጠሩ አዳዲስ ለውጦችን እና የዘርፎችን መስፋፋት በበቂ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ አለመሆናቸውን ገልጿል።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር አቶ በረከት ፍስሐጽዮን የቀድሞው የኢኮኖሚ መለኪያ የዲጂታል የገንዘብ ልውውጦችን፣ እንደ ካፒታል ገበያ፣ የበጋ መስኖ ልማትና የኮሪደር ልማት ያሉ አዳዲስ የኢኮኖሚ ልማቶች መረጃዎች ያልተካተቱበት፣ አዲስ የኢኮኖሚ ቅርፅ በአሮጌ መለኪያ ሲለካ የቆየበት መሆኑን ተናግረዋል።
አዲሱ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ኢኮኖሚ ሥሌት በቅርቡ የተካሄዱ የግብርና ቆጠራን፣ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራን እና የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት መረጃዎች የተካተተበት ወቅታዊ የሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታን የሚያመለክት መሆኑን ገልጸዋል። በአዲሱ ስሌት የኢትዮጵያ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 210 ቢሊዮን ዶላር መድረሱም ተገልጿል።
ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት አንድ ሀገር በተወሰነ ጊዜ፣ በአብዛኛው በአንድ ዓመት በሀገር ውስጥ ያመረታቸውን ሁሉንም የመጨረሻ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች በገበያ ዋጋ የሚለካ ኢኮኖሚያዊ መለኪያ ነው።
በዚህ መለኪያ ውስጥ የቤተሰቦች ፍጆታ፣ የንግድ ተቋማት እና የግል ባለሐብቶች ኢንቨስትመንት፣ የመንግሥት ወጪ እንዲሁም ከወጪ ንግድ የሚገኘው የተጣራ ውጤት ተደምረው ይሰላሉ። (ሚንበር ቲቪ)












