በአውሮፓ እና በአሜሪካ በ30 ሀገሮች ውስጥ ዘረኝነትንና የእስልምና ጠልነትን ያስፋፉ የተቀናጁ የማስታወቂያ ዘመቻዎች ሁለት ምሁራን ለሦስት ዓመታት ባደረጉት ምርመራ ተጋልጧል።
ሁለት ምሁራን ባደረጉት ምርመራ፣ ዘረኝነትን፣ የእስልምና ጠልነትንና ኢላማ የተደረገችው ኳታርን የሚጻረሩ አመለካከቶችን ለማስፋፋት ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት ዲጂታል ተፅዕኖ የመፍጠር ዘመቻ መኖሩን ይፋ አድርገዋል። ማስረጃዎቹ ዘመቻው እስራኤልን ለማገልገል ብሔራዊ ጥቅሞቿን ከማስጠበቅ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
በኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የዶሃ ካምፓስ ፕሮፌሰር ማርክ ኦወን ጆንስና የግል ተመራማሪው ሶሃን ዳሱዛ “ማኑፋክቸሪንግ ዘ ግሬት ሪፕሌስመንት”በሚል ርእስ ባወጡት ሪፖርት፣ ዘመቻው ቢያንስ 11 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደወጣበትና በአውሮፓ፣ በአሜሪካና ሊባኖስን ጨምሮ በ30 ሀገሮች እንደተካሄደ ይገልጻል። ተመራማሪዎቹ ዘመቻውን እስካሁን ከተመዘገቡ ትልልቅ የዲጂታል ተፅዕኖና የሐሰት መረጃ ዘመቻዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።
አልጀዚራ እንደዘገበው፣ ከጥቅምት 2016 እስከ ጥቅምት 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ ሙስሊም ጠል፣ ስደተኛ ጠል፣ ዘረኛና ፀረ-ኳታር የሆኑ ማስታወቂያዎች ቢያንስ 533 ሚሊዮን ጊዜ ታይተዋል። ማስታወቂያዎቹ በዩቲዩብ፣ በቲክቶክና በፌስቡክ ለበርካታ ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ደርሰዋል። ከጠቅላላው የዘመቻው ማስታወቂያዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛ ያህሉ በፈረንሳይ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ከሁሉም ሀገሮች ከፍተኛው ድርሻ የያዘ ነው። ማስታወቂያዎቹ በብሪታንያ በ154 ሚሊዮን ጊዜ ሲታዩ፣ በአሜሪካ በ100 ሚሊዮን በመታየት ሁለተኛ ሆናለች።
ዘመቻው በፈረንሳይ እንዴት ተግባራዊ እንደተደረገ ሲተነትን፣ “የዘመቻው ደጋፊዎች የሚለቋቸው ማስታወቂያዎች ታሪካዊ ትንተና እንደሚያሳየው በተደጋጋሚ ከምርጫ ሰሌዳዎች ጋር ለመስማማት ሞክረዋል” ሲል ገልጿል። በተለያዩ ሀገሮችም የምርጫ ቀን ሰሌዳ ጋር በሚገጣጠም መልኩ ሲለቀቁ እንደነበር አሳይቷል።
ተመራማሪዎቹ እንዳሉት፣ በአውሮፓ ማስታወቂያዎቹ በሴራ ንድፈ ሐሳብ መዋቅር ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ይህም ነጮች በስደተኞች እየተተኩ ነው የሚል ሐሳብ የሚከናወን ሲሆን፤ በዘመቻው ኳታር፣ በፀረ አይሁድ የሴራ ትርክቶች አውሮፓን “እስላማዊ” ለማድረግ የሙስሊሞችን ፍልሰት በስውር የምታስተባብር ኃይል ተደርጋ ተስላለች። በቲክቶክ ለአውሮፓ ተጠቃሚዎች በኢራን የመንግሥት ለውጥ እንዲደረግ የሚያበረታታው የዘመቻው አንዱ ክፍል እንደነበር ተጠቅሷል። ማስታወቂያዎቹ መታየት የጀመሩት አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱበት የካቲት 21/ 2018 አራት ቀን ቀደም ብሎ ነው።












