የፓኪስታን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የሸሪዓ መርሆችን የሚያሟሉ አክሲዮኖችን መገበያየት የሚያስችል የንግድ መድረክ ይፋ አድርጓል። ይህም በሀገሪቱ እስላማዊ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ይበልጥ ተደራሽ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ርምጃው የመጣው የሀገሪቱ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት እ.አ.አ. በ2022 መንግሥት በወለድ ላይ የተመሠረተ የባንክ እና የፋይናንስ ሥርዓትን እስከ ቀጣዩ የአውሮፓውያን 2027 ዓመት ድረስ እንዲያስወግድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ተከትሎ ነው።
ዐረብ ኒውስ እንደዘገበው፣ ሐሙስ ዕለት ይፋ በሆነው የአክሲዮን የግብይት መድረኩ 39 ሰነደ ሙዓለ ንዋይ አገበያዮች ሸሪዓን መሠረት ያደረገ አገልግሎት በመስኮቶች በኩል ለመስጠት ተመዝግበዋል። እንዲሁም ሁለት ተጨማሪ አገበያዮች ሙሉ በሙሉ ሸሪዓን መሠረት ያደረጉ ደላሎች በመሆን ፈቃድ ማግኘታቸው ተገልጿል።
በፓኪስታን በዘርፉ በተደነገጉ የአሠራር ሂደቶች እና ደንቦች የሚተዳደር እንደሆነ የተገለጸው የአክሲዮን ገበያው፤ ግብይቱም እንደ የመንግሥት ኢጃራ ሱኩክ እና የኮርፖሬት ሱኩክ ላሉ ሸሪዓን መሠረት ላደረጉ አክሲዮኖች ብቻ የተገደበ ነው ተብሏል።
የሸሪዓ መርሆችን መሠረት ያላደረጉ እና በወለድ ላይ የተመሠረቱ የብድር አገልግሎቶች መታገዳቸውም የተገለጸ ሲሆን፣ እንደ ሙራባሃ ሼር ፋይናንሲንግ ያሉ ሸሪዓን መሠረት ያደረጉ አማራጮች መቅረባቸውም ተጠቅሷል። አዲስ የተዘጋጀው የመገበያያ መድረክ እያንዳንዱን ሸሪዓን መሠረት ያደረገ አክሲዮን እና ሱኩክ በዝርዝር እንደሚያስቀምጥ ተገልጿል።
በፓኪስታን እስላማዊ ፋይናንስ ዘርፍ የባንኮች ሐብት እና ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ አንድ አራተኛውን ይይዛል። እንዲሁም ለሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ከተዘረዘሩት አክሲዮኖች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሸሪዓን ሕግ የሚያሟሉ ናቸው። (ሚንበር ቲቪ)












