ደራሲ ኸድር ታጁ “ዐድዋ የትብብርና የድል ምልክት – የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተሣትፎ እንደማሳያነት” የሚል ርእስ ያለውን መጽሐፉን በነገው እለት ለአንባቢያን እንደሚያቀርብ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግሯል፡፡ ደራሲው እንዳለው፣ የመጽሐፉ ጥቅል ይዘት “በኢትዮጵያ የነጻነት ታሪክና ገድል ውስጥ አንጡራ በኾነው የዓድዋ ድል የተሳተፉ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አሻራ የሚዳስስ ነው”፡፡ በዚህም ከ39 በላይ አርበኛዎችን በሥም ደረጃ፣ የ19 አርበኛዎችን የተሣትፎ ገጽታ በውስን ዝርዝር ለመቃኘት ሙከራ ተደርጓል፡፡
በ162 ገጽ የተጠናቀረውን መጽሐፍ ለማዘጋጀት “ከፍተኛ የደረቅ መረጃ ውስንነት” እንደነበር የገለጸው ኸድር ታጁ፣ የዝግጅት ሒደቱ ከ12 ዓመት በፊት እንደተጀመረም አስታውሷል፡፡
አዲሱ መጽሐፉ የትውልድን ሥነ ልቡና ለማጎልበት፤ ትናንት “የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አያቶች” በጋራ የሠሩትን ታላቅ ድል፤ “ዛሬም አዲሱ ትውልድ በተባበረ ክንድ፣ በአዲስ መልክና አድማስ እንዲደግፍ” ተስፋ በማድረግ የታሪክ ሥነ ዘዴን መሠረት አድርጎ የተሰናዳ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ አንባቢያንም “በትኩረት እንዲያነቡትና የይዘት ዓላማው ለእኔ ትውልድ እንዲሰርጽ እመኛለሁ” ሲል በ“ሚንበር ቲቪ” በኩል ለመጽሐፍ ወዳጆች መልእክት አስተላልፏል፡፡
“ዐድዋ የትብብርና የድል ምልክት” ከነገ ጀምሮ ለገበያ የሚቀርበው በተለያዩ መጻሕፍት መደብሮች እንደሚሆንም ገልጿል፡፡
ኸድር ታጁ ከዚህ ቀደም “ዓምደ ሀገር – ሸይኽ ዓሊ ጎንደር”፣ “ዳናዎቹ ቅጽ 1”፣ “ዳናዎቹ ቅጽ 2”፣ “ሸይኽ ሰይድ ኢብራሂም – የሸይኽ ጫሌ አንጸባራቂ ታሪክ”፣ “የበጌ ምድር አራጣ ሊቃውንት (ዑለማዎች)” እና “አግራሞታዊ ጉዞ” የተባሉ መጻሕፍትን በማዘጋጀት ይታወቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












