ኸድር ታጁ ባለፉት ዓመታት ለግሉ ብቻ የተሠጠው በሚመስል የአጻጻፍ ሥልት ያለማቋረጥ የታሪክ መጽሐፍትን በማቅረብ ላይ የሚገኝ ጸሐፊ ነው፡፡ “ዓምደ ሀገር – ሸይኽ ዓሊ ጎንደር”፣ “ዳናዎቹ ቅጽ 1”፣ “ዳናዎቹ ቅጽ 2”፣ “ሸይኽ ሰይድ ኢብራሂም – የሸይኽ ጫሌ አንጸባራቂ ታሪክ”፣ “የበጌ ምድር አራጣ ሊቃውንት (ዑለማዎች)” እና “አግራሞታዊ ጉዞ” ከሥራዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ በተያዘው ዓመት ጥቅምት 9/2018 ከምድር ሕይወት የተለዩትን የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ በማጠናቀቅ ለአንባቢያን ሊያደርስ መሆኑን አሳውቋል፡፡ የሚንበር ቲቪው አሕመድ ዓብዱረሕማን ስለ አዲሱ መጽሐፍ ላቀረበለት ጥያቄ ምላሹን በጽሑፍ ሰጥቷል፡፡ መልካም ንባብ፡-
- ባለፉት ዓመታት በርካታ መጽሐፍትን አዘጋጅተሃል፤ መጀመርያ እንዲህ ዐይነቱን ግዙፍ ሥም ያለውን ሰብዕና ታሪክ ልታዘጋጅ መሆኑን ስታውቅ ስሜትህ ምን መሣይ ነበር? ‘እንዴት ልወጣው ነው’ የሚል ከኃላፊነት የሚመነጭ ፍርሐትና ጭንቀት ወይስ ሌላ? …በስሜትም ሆነ ከግዝፈቱ አንጻር ከሌሎች ሥራዎችህ በምን ይለያል?
ታሪካዊ ዕድል ነውና፤ አስቀድሞ በውስጤ የናኘው ደስታ ነው፡፡ በማስከተል ቢያንስ አርባ ዘጋቢ ፊልሞች የተሠራላቸው የአደባባይ ሰብዕና በመኾናቸው፤ ከግለ ታሪክ ሥነዳ ባሻገር “ያልተገለጠ ገጽታ የመግለጥ” አስፈላጊነት፣ ከዕድሜ መግፋት ጋራ የተያያዘው የጤና እክልና ተፈላጊው የመረጃ ልውውጥ ጉዳይ ተጨምሮ አሳስቦኝ ነበር። በፈታኝ የሕይወት ውጣ ውረድ፣ በውስብስብ ማኅበራዊ ጉዞና ብሔራዊ አገልግሎት የፈሰሰ፣ በአራት መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ የተቀዳ፣ ድፍን ሀገር ቅቡልነት የቸረውን ዝርግ ኑረት በወጉ ስለመሠነድ አስቤም ቆዝሜያለሁ።
እኒህ ሰብዕና ለዚህ ትውልድ በዓይነ ሥጋ እና በቅርበት የሚታወቁ፤ ያለ ሃይማኖት፣ ያለ ጎሣ እና ቋንቋ፣ ያለ የፖለቲካ ፍላጎት ልዩነት በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የተደነቁ፤ ብሔራዊ ምልክት ኾነው የተሰነደቁ፤ በርካታ ዐሥርት ዓመታትን በአገልግሎት ያሳለፉ፣ ዓለም አቀፉ ዕውቅና ያተረፉ፤ መጠነኛ የታሪክ መረጃ ሐብት ያስቀመጡ መኾናቸው የመጽሐፉን ገጽታ የተለየ እሴት ጨምሮለታል።
- ለመጽሐፉ የሰጠኸው ርእስ “የሀገር መልክ” የሚል ነው፤ ይህን ርእስ ለምን መረጥክ?
ኢትዮጵያ ሠፊ መልክዓ ምድር፣ ብዝኃ ብሔረ ሰቦች፣ የቋንቋዎችና የሃይማኖቶች ክምችት፣ ውትብትብ የታሪክና የፖለቲካ ቅራኔዎች የታመቁባት ሀገር ናት። በውስጧ ያሉ ኅብር ዜጎች ከልዩነታቸው ጋር በ“ኢትዮጵያዊነት” ጥላ ሥር ይሰባሰባሉ። ይኽ አሰባሳቢ መልክ የኢትዮጵያ (የሀገር) መገለጫ ነው።
በታሪክ አጋጣሚ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለመሰብሰብ የጣሩ፣ ያለ ልዩነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በምክረ ሐሳብና ገቢራቸው እንዲሁም በኅልፈታቸው ወቅት የተሰባሰበባቸው ዋርካ ናቸው። ይህ የአሰባሳቢነት ፀጋ የሀገር ዋና መገለጫና “መልክ” ነው። ተቀዳሚ ሙፍቲን የሁላችን ያደረገው ይኸው ነው፡፡ በእነዚህ ትስስሮች ምክንያት እና በተቀዳሚ ሙፍቲ ኅብር አበርክቶት ሚዛን “የሀገር መልክ” እንዲሰኙና መጽሐፉም ርእሱን እንዲዋስ ገድዷል።
- የመጽሐፉን መረጃዎች የመሰብሰብና የማጣራት ሒደቱ ምን ያህል ጊዜ ወሰደ? ስለ መጽሐፉ ጥቂት ንገረን…
ለመጽሐፍ ዝግጅቱ ተቀዳሚ ሙፍቲን በሕይወት በማግኘቴ በአምስት ወር ውስጥ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ለማስመረቅ በዕቅድ ተይዞ ቢጀመርም በሦስተኛው ወር በድንገት ሕይወታቸው አለፈ። ይሁን እንጂ የመጽሐፉ ቀዳሚ ሙሉ ረቂቅ በሙሉ ጊዜ በየቀኑ 17 ሰዓታት ተሰጥቶት በመዘጋጀቱ ከተያዘው ጊዜ ቀድሞ በአራተኛው ወር ተጠናቋል፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረው የእርማት ሥራ በቤተሰባቸውና በአስተባባሪ ኮሚቴው ሲሠራ አንድ ወር ፈጅቷል፡፡ እርምት ተከላውና ቀሪ የትየባ ልማቱ ደግሞ አንድ ወር ወስዷል። ኅትመቱ በተለያየ ምክንያት እስካሁን ቢዘገይም የመጽሐፉ ዝግጅት በስድስት ወር ገደማ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡
በ505 ገጽ የተዋቀረው መጽሐፍ እንደ አንድ የሕይወት ታሪክ ከመሠናዳቱ ባሻገር በርካታ የዘመን ገጽታዎችን፣ ጉልሐንን፣ ተቋማትን፣ ማኅበራዊ የወል እሴቶችን፣ ብሔራዊ ገጽታዎችን፣ ከወሎ ቦረና ዳሎታ እስከ ሰፊው አፍሪቃ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጉዳዮች በሰበዝ ተቀናጅተው ይዘቱ ተጠናቅሯል፡፡
- በታሪኩ ዝግጅት ወቅት ስለ ተቀዳሚ ሙፍቲ አንተ ቀድመህ የማታውቀውና በሥራ ሂደት ያወቅከው በጣም ያስገረመህ ነገር የትኛው ነው?
ዝግጅቱን ስጀምር በርካታ መረጃ እንዳለኝ አምኜ ነበር፤ በርግጥም ነበረኝ። ምክንያቱም የመምሕራቸውን የሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብን ታሪክ ስጽፍ ታሪካቸውን ቃኝቸዋለሁና! ከዚያም ለግለ ታሪካቸው ዝግጅት ተቀዳሚ ሙፍቲን አራት ጊዜ ቃለ መጠይቅ አደረግኩ። ረዥሙ ቆይታችን 3 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ወስዷል። ከአብራክ ልጆቻቸው ሸሽገው ያስቀመጡትን በዓረቢኛ ቋንቋ የጻፉትን ግለ ታሪክ በልጆቻቸው ፊት ለጥናት ሰጥተውኛል፤ ሌላም ሠነድ ተጋርቻለሁ። በዚህ ሒደት ብዙም ሳልዘልቅ፣ ሙሉ ታሪካቸውን ሳደምጥ ፍጹም አዲስ እንግዳ እና ተደማሚ ሰው ሆኜ ቀጠልኩኝ፤ በዚህም እገረማለሁ።
- በመጽሐፉ ይበልጥ እንዲጎላ የተደረገው የትኛው የሕይወታቸው ክፍል ነው?
የመጽሐፍ ዝግጅቱ በአንድ ገጽታው መሠረታዊ የታሪክ ሥነ ዘዴን ተከትሏል። በዚያም ምክንያት የርእሰ ጉዳዮች ሥፋት ወይም መጉላት በመረጃ ምንጮች አቅምና ልክ የተገነባ ነው። በተቻለ መጠን ሁሉንም የሕይወት ገጽታ በወጉ ቅርጽ ሰጥቶ ለመሠነድ ሙከራ ተደርጓል፡፡
- እንደ ተቀዳሚ ሙፍቲ ዐይነቱ በእድሜም በእውቀትም የገዘፈ ሰው ታሪክ ሲጻፍ ሩጫው በዋነኝነት የሚሆነው ከጊዜ ጋር እንደሚሆን መገመት ይቻላል፤ ይህን ሒደት እንዴት ትገልጸዋለህ? በዚያውም ታሪካቸውን ስትጽፍ ትልቁ ፈተና ምን ነበር?
በዋነኝነት የሀገር ባለውለታዎችን በሕይወት እያሉ፤ እንደ ሀገር በተለይም እንደ ሙስሊም ማኅበረሰብ ምሥጋና ማቅረብ አልተለመደም፤ ታሪካቸውን መሠነድም ትኩረት አይሰጠውም። የተቀዳሚ ሙፍቲ መጽሐፍ ዝግጅት ይህን ጎታች ባሕል ለመቅረፍ የታቀደበት ነበር። ስለኾነም በተጨባጫችን ቁጭቱ አለኝ፣ የባሕል ሽረቱ ውስጥ የመሳተፍ ዓላማ ስለነበረኝ፤ በታሪክ አጋጣሚ ዐቢዩ የፈጻሚነት ልጓም ደግሞ ሲሰጠኝ ይህን ለማሳካት ለወራት በየቀኑ 17 ሰዓታት ከመጻሕፍ ዝግጅቱ ጋር በደስታ አሳልፌያለሁ። ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ማስተዋል የሚገድበት ሩጫ ውስጥ ስተጋ ቆይቻለሁ።
ሆኖም በመካከል የተቀዳሚ ሙፍቲ ቀላል የሚባሉ ሕመሞች ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ዕቀባ ያስከትላሉ። ተቀዳሚ ሙፍቲ በስተርጅና ዘመናቸውም ቢሆን ለማኅበራዊ ሕይወት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ስለነበር በተለያየ ጉዳይ ከቤት ይወጡ ነበር። ጥያቄ፣ ቁጭትና ጉጉት ይዤ መጠበባቅ ስሜትን ይፈትን ነበር። የዝግጅቱን ውስን አቅጣጫ ከተገነዘቡ በኋላ ግን ‹‹ምነው ጠፋህ?›› ወደማለት ቀረቡልኝና በጥሩ ሁኔታ ሄድን። ሌሎች እርሳቸው የጠቆሙኝ መረጃ ሰጭዎች ግን ከሞላ ጎደል የጊዜ ነጻነት፣ መረጃ የመለዋወጥ ተነሳሽነት አልነበራቸውም። ይህን ተቋቁሜ ያገኘኋቸው አንጻራዊ መረጃ አካፍለውኛል።
ከሙፍቲ ኅልፈት በኋላ የተጋጠምኩት ደግሞ ከሌላ ጣጣ ጋር ነው፡፡ ለዝግጅቱ በሰጠሁት ሙሉ ትኩረትና በምኖርበት አካባቢ የአየር መለዋወጥ ምክንያት፣ ረፍት የሚፈልገውንና ነጻነት የማይለግሠውን የሳምባ ምች ሕመም ሸምቼ ነበር። “ሳልጨርሰው አልሞትም” እያልኩ በዚሁ ሕመም ውስጥ ለመጽሐፉ ዳርቻ ግብግብ አካሄጃለሁ። አልሐምዱሊላህ! በሒደት ሕመሜ ፈውስ፣ መጽሐፉም ፍጻሜ አግኝቷል፡፡
- ከእርሳቸው ጋር በነበረህ ቆይታ አይረሴ የምትለውን ገጠመኝ ብትነግረኝ?
ተቀዳሚ ሙፍቲ ለበርካታ ሚዲያዎች ግለ ታሪካቸውን ስለሰጡ፣ ብዙ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ዘጋቢ ፊልሞች ስለተሠራላቸው፣ የመጽሐፍ ዝግጅቱ ከዚያ የተለየ እንደማይኾን በመገመት እምብዛም ትኩረት አልሰጡትም ነበር። ለመጀመር ስንነጋገር፦ “አጀብ…የተናገርኩት እኮ በየቦታው አለ፤ እርሱን መሰብሰብ ይቻላል፤ እንዲያው ልጠይቅ ካልክም እንጠያየቃለን ወይም ሰዎችን ጠቁምሃለሁ›› ብለውኝም ነበር፡፡
በዚሁ መንፈሥ፣ ጊዜ ወስጀ የቃለ መጠይቅ ቅጽ አዘጋጅቸ ደጅ ጠናሁ። እርሳቸውና እኔ ብቻ ቤታቸው ውስጥ በአንድ ክፍል ተቀመጥን። ጥያቄው እያሳሳቀ ስቦ ሲያስገባቸው ይታየኝ ነበር፡፡ አዕምሯቸው ማሕደሩን አንቅቶ ማዕዱን ከፈተ፤ ይህን ጊዜ ውስጤ በሐሴት ተንቦጨቦጨ፤ ያን ቀን ድንገት መሽቶ ወጣሁ።
ከቀናት በኋላ መስከረም 1/2018 በድጋሚ አገኘኋቸውና ቤታቸው በረንዳ፣ እርሳቸው በወንበር እኔ ወለል ላይ ተቀምጬ ጭውውት ጀመርኩ። በሕይወቴ ረዥም ሰዐት ያነጋገርኩት፣ ያዳመጥኩት፣ ያን ዕለት ነበር። እርሳቸውም አያሌ ውሐ ያልነካቸውን የሕይወት ፋናዎች፣ ገጽታና የታሪክ መረጃዎች በረዥም ሰዐታት ያካፈሉት ያን ጊዜ ይመስለኛል፤ ያለምንም ፋታ ቆይታችን 220 ደቂቃ ገደማ የፈጀ ነበር። ያን ዕለት ብዙ ስቀዋል፣ ብዙ አልቅሰዋል፣ ብዙም ተክዘዋል፤ ለእኔም ጎላ ብሎ የሚታወሰኝ ሆኖ አልፏል፡፡
- መጽሐፉ ለአንባቢያን መቼ ይደርሳል?
ከቀናት በኋላ የኅትመት ሒደቱን እንደሚጨርስ ተስፋ አለኝ። የመጻሕፉ አሳታሚና ባለቤት ቤተሰባቸው ነው። በሽያጭ ገቢው የተቀዳሚ ሙፍቲን “ሐሪማ” (የልኅቀት ማዕከል) የማልማት ዓላማ አላቸው። ልዩ የምረቃ ሥነ ሥርዓትም ለማዘጋጀት በእቅድ ተይዟል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












