ዑጋንዳ ለምሥራቅ አፍሪካ እና ለሠፊው የአፍሪካ ገበያ ዋና የሐላል ማዕከል ለመሆን የምታደርገው ጥረት አካል ነው የተባለውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው ብሔራዊ የሐላል ማረጋገጫ ሥነ ምሕዳር ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ይፋ አድርገዋል፡፡
በዑጋንዳ ብሔራዊ የደረጃዎች ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ጀምስ ካሲግዋ የሚመራው ይህ እንቅስቃሴ፣ የሐላል ማረጋገጫን ከመደበኛ መስፈርትነት ባለፈ “ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለእሴት ጭማሪ እና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ” እንደ መሣሪያ ለመጠቀም ያለመ ነው፡፡
ለዚሁ እንዲያግዘው በሐላል ማረጋገጫ ከምትታወቅው ከማሌዥያ የሐላል ልማት ኮርፖሬሽን ባለሞያዎችን በመጥራት በሐላል ሥነ ምሕዳር፣ መሠረተ ልማት እና የሕግ ማዕቀፍ ላይ ግምገማ እያደረጉ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
የሐላል ሰርተፍኬት አንድ ምርት፣ አገልግሎት ወይም የንግድ እንቅስቃሴ የሸሪዓ ሕጎችን ያከበረ እና ለሙስሊሞች ጥቅም ላይ እንዲውል ወይም ለመመገብ የተፈቀደ (ሐላል) መሆኑን የሚያረጋግጥ ኦፊሴላዊ አሠራር ነው፡፡ የዐለም አቀፉ የሐላል ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት 7 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን፣ ከአራት ዓመት በኋላ ከ10 ትሪሊዮን ያልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የዑጋንዳ ባለሥልጣናት ሀገሪቱ ያላት የግብርና እና የእንስሳት ሐብት፣ በምሥራቅ አፍሪካ ካላት ስትራቴጂካዊ ቦታ ጋር ተደምሮ እያደገ ከመጣው የሐላል ዘርፍ ገበያ ትልቅ ደርሻ እንድታገኝ ያስችላታል ብለው ያምናሉ፡፡ ሀገሪቱ በምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ብቸኛዋ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት (ኦአይሲ) አባል ሀገር በመሆኗ ከፍተኛ የሙስሊም ቁጥር ያላቸውን ገበያዎች በቀላሉ እንድታገኝ እንደሚያስችላት የዑጋንዳ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም 57 አባል ሀገራትን ባቀፈውና ለእስላማዊ ገበያዎች የሚያስፈልጉ ደረጃዎችን በሚያዘጋጀው የኦአይሲ የእስላማዊ ሀገራት የደረጃዎች እና ትንበያ ኢንስቲትዩት ውስጥ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች፡፡
የሐላል መረጋገጫው ማዕከሉ ከመከፈቱ በፊት ሀገሪቱ ለትግበራ እንቅፋት የሚሆኑ ሕጎችን ለማሻሽል እየሰራች እንደምትገኝም ተገልጿል፡፡ የዑጋንዳ ንግድ ሚኒስትር ጀነራል ዊልሰን ምባሱ፣ ሀገራቸው “ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ መግባት ብቻ ሳይሆን፣ ገበያው ውስጥ ዘልቆ መቆየት ላይ” ትኩረት ማድረግ አለባት ብለዋል፡፡ ከሐላል ምርት እና ማረጋገጫ ጋር የተያያዙ ሕጋዊ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የዑጋንዳ የሕግ ማዕቀፍ እንዲከለስ ጠይቀዋል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ ማማ ምባባዚ፣ እንቅስቃሴው በተለይም ዑጋንዳ የኢኮኖሚ ዕድገቷን ለማፋጠን በምትጥርበት በአሁኑ ሰዐት መምጣቱ ተስማሚ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡ “ሐላል ማረጋገጫ የሀይማኖት ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ የንግድ እና ኢኮኖሚ እድልም ጭምር ነው፤ ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ መቅረት አንችልም” ብለዋል፡፡
ዑጋንዳ በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ የ4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ግብርና እና የምግብ ምርቶችን ወደ ውጭ የምትልክ ቢሆንም፣ ወደ ባሕረ ሰላጤው ገበያ የሚደርሰው ግን ከ10 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ ባለሥልጣናት በአዲሱ የማረጋገጫ ሥርዐት አማካኝነት በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች፣ ሳዑዲ ዐረቢያ፣ ኦማን፣ ኩዌት፣ ባህሬን እና ቀጣርን ወደሚያቅፈው ወደ ገልፍ ሀገራት የሚላከውን የግብርና ምርት ኤክስፖርት በእጥፍ ለማሳደግ አቅደዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












