Homeዜናና ወቅታዊዜና1 ሺሕ 300 ዐመታት የሚጠጋ የእስልምና ታሪክ በአንድ ሠንዶ የያዘ ዲጂታል አትላስ...

1 ሺሕ 300 ዐመታት የሚጠጋ የእስልምና ታሪክ በአንድ ሠንዶ የያዘ ዲጂታል አትላስ ይፋ ተደረገ

ከመልክዐ ምድር፣ ሥርወ መንግሥት፣ ከሊቃውንትና ከታሪካዊ ክስተቶች ጋር በማጣመር ወደ 1 ሺሕ 300 ዓመታት የሚጠጋ የእስልምና ታሪክ የሚያቀርብ ዲጂታል አትላስ ይፋ ተደርጓል፡፡

አትላሱ “የእስልምና ታሪክ አትላስ” በሚል ሥያሜ በislamicatlas.org ድረ ገጽ ላይ ቀርቧል፡፡ እ.አ.አ ከ632 እስከ 1924 ያለውን የእስልምና ዓለም የሚሸፍነው ይህ አትላስ፣ ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ መረጃዎችን በአንድ ካርታ ላይ አቀናጅቷል፡፡ በአትላሱ የተጠቀሰው ጊዜ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ኅልፈት እስከ አል ኺላፋህ ዑሥማኒያህ (ኦቶማን ኸሊፋ) ማብቂያ ያለውን የእስልምና ታሪክ የሚሸፈን ነው፡፡

በቱርክ በሚገኘው የሰልቹክ ዩኒቨርሲቲ ምሑራንና የቲ ኮፐርስ ዲጂታል ማዕከል የተዘጋጀው ፕሮጀክት፣ የታሪክ መረጃዎችን በጊዜ ሠሌዳ (Timeline) እና በመረጃ ንብርብሮች (Layers) አቀናጅቶ ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመድረኩ ላይ ከተካተቱት ዋና ዋና የመረጃ ስብስቦች መካከል የ186 የእስልምና ሥርወ መንግሥታት እና 830 መሪዎች ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ከ14 ሺሕ በላይ ሊቃውንት የሕይወት ታሪክ ተሠንዷል፡፡

ከታዋቂው የእስልምና ዓለም የታሪክ እና የመልክዐ ምድር ምሑር ያቁት አል ሐመዊ በ13ኛው ክፍለ ዘመን ከተዘጋጀው የሀገራት እና የቦታዎች ኢንሳይክሎፒዲያ የተወሰዱ 12 ሺሕ 954 የመልክዐ ምድር መዝገቦች፣ 3 ሺሕ 458 የሣንቲም ማዕከላት፣ 2 ሺሕ 49 ሥፍራዎች፣ 801 የሕንጻ ቅርሶች በአትላሱ ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡ በ14ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው በዓለም ታሪክ ውስጥ ታዋቂው ሞሮካዊ ምሑር፣ ተጓዥ እና የታሪክ ጸሐፊው ኢብን ባቱታ እና በአል ኺላፋህ ዑሥማኒያህ ታሪክ ውስጥ እጅግ ታዋቂው ቱርካዊ ተጓዥ፣ የታሪክ ጸሐፊ እና የመልክዐ ምድር ተመራማሪ የኤቭሊያ ቸለቢ የጉዞ ማረፊያዎችም ተካተዋል፡፡

የመድረኩ አሰናጅ ዶክተር ሑሴን ኮጋልፕ እንደገለጹት፣ አትላሱ በቀላሉ ካርታዎችን ከማሳየት ባለፈ በታሪካዊ ግለሰቦች፣ በመምሕርና ተማሪ እንዲሁም በሥርወ መንግሥታት መካከል የነበሩትን ባለብዙ ንብርብር የግንኙነት መረቦች ግልጽ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በዲጂታል ዘዴዎች አማራጭ የታሪክ ሒደቶችን ለመመርመር ያስችላል፡፡

አናዶሉ ኤጀንሲ እንደዘገበው፤ አትላሱ ሙሉ ለሙሉ ክፍት ተደርጎ ስለለማ፣ ተመራማሪዎችና ምሑራን መረጃዎችን በማውረድ ለአዳዲስ ጥናቶች መጠቀም ያስችላቸዋል፡፡ በዐረቢኛ፣ በእንግሊዝኛ በቱርክኛ ቋንቋዎች አገለግሎት ለሚሰጠው መድረክ በቀጣይ የሞባይል መተግበሪያ እንደሚዘጋጀለት ተገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular