Homeዜናና ወቅታዊዜናሀገር አቀፍ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ስትራቴጂ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ

ሀገር አቀፍ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ስትራቴጂ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ላለው ከወለድ ነጻ ፋይናንስ ብሔራዊ የወለድ ነጻ ፋይናንስ ስትራቴጂ የዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ አስታውቋል። በኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገዥነት የሚተዳደረው ማዕከላዊ ባንኩ፤ ከወለድ ነጻ ፋይናንስ ለመቆጣጠር እና ለመምራት የሚያስችል ነው የተባለውን ስትራቴጂ እያዘጋጀ የሚገኘው ወይዘሮ ሒክመት ዐብዱላሂ ከሚመሩት ኤፍ.ኤስ.ዲ ኢትዮጵያ ጋር በአንድነት ነው፡፡

ስትራቴጂው ከሸሪዓ ጋር ተስማሚ የፋይናንስ ሥርዓት፣ ሱኩክ እና ብሔራዊ የሸሪዓ ቁጥጥር እንዲኖር የሚያግዝ እንዲሁም ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ግብር እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል። ስትራቴጂው ወደ ተግባር ሲገባ በመደበኛው ባንኮች የሚገኙ ትላልቅ ከወለድ ነፃ አገልግሎት መስኮቶች ወደ ሙሉ የወለድ ነፃ ባንኮች እንዲቀየሩ መንገድ የሚጠርግ ይሆናል ተብሏል።

ባለፈው ሣምንት በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በተካሄደው ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ስትራቴጂ ሁለተኛ ዙር የማረጋገጫ ወርክሾፕ ላይ የተገኙት የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ፤ በሒደቱ ግልጽ ቅደም ተከተሎች፣ የተቀማት ኃላፊነቶች፣ የጊዜ ሠሌዳዎች እና ሊመዘኑ የሚችሉ ውጤቶችን የያዘ ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅ አሳስበዋል፡፡ ድጋፍ ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ምክትል ገዥው ምን መቀየር እንዳለበት፣ ማን ርምጃ መውሰድ እንዳለበት፣ በምን ቅደም ተከተል እና ሐብት መከናወን እንዳለበት በግልጽ መቀመጥ አለበት ብለዋል። ከወለድ ነፃ ፋይናንስ፤ የፋይናንስ አካታችነትን እንደሚያሰፋ ጠቅሰው እድገቱ በተጠናከረ ሕግ፣ ውጤታማ ቁጥጥር፣ ጠንካራ የሸሪዓ አስተዳደር እና ተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ከስትራቴጂው ዋና ዋና ሐሳቦች አንዱ የግብር እኩልነት ሲሆን ከወለድ ነፃ ፋይናንስ የሚጠቀሙ ደንበኞች ከመደበኛው ብድር ተጠቃሚዎች በላይ ከፍተኛ ታክስ እንዳይከፍሉ ለማድረግ ያለመ ነው።

በስትራቴጂው መሠረት ከብሔራዊ ባንክ በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስር የሚመራ ሀገራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ የሚዋቀር ሲሆን፣ የባንኮች የሸሪዓ አማካሪዎች የበላይ የሆነ ብሔራዊ የሸሪዓ ተቆጣጣሪ ቦርድም ይቋቋማል፡፡

ስትራቴጂው በብሔራዊ ባንክ ውስጥ “ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ክፍል” እንዲቋቋም ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ክፍሉ የሕግ ረቂቆችን በማዘጋጀት፣ የሸሪዓ ውሎችን እና ስጋቶችን በመቆጣጠር ረገድ የቁጥጥር አቅምን የመገንባት ኃላፊነት እንደሚሰጠው ተገልጿል። የኤፍ.ኤስ.ዲ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሒክመት ዓብዱላሂ በሐምሌ ወር በተካሄደው ሐላል ቢዝነስ ፎረም ላይ የብሔራዊ ስትራቴጂው ተጠናቆ በመስከረም ወር ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመው ነበር።

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ31 ባንኮች መካከል በ23ቱ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ አራቱ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ ባንኮች ናቸው፡፡ 21 ያህሉ ደግሞ አገለግሎቱን በተለዩ መስኮቶች ያቀርባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ ባለሞያዎች ማኅበር ጋር በመተባበር በሚያዝያ ወር ባዘጋጀው ሦስተኛው ሀገራዊ የሸሪዓ አማካሪዎች ጉባኤ ላይ እንደተገለጸው፣ በተያዘው ዓመት ከወለድ ነጻ የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ30 ሚሊዮን አካውንቶች 514 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በሥራ ላይ ያለው ከወለድ ነጻ የፋይናንስ አቅርቦት 151 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከዚህም ውስጥ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 297 ቢሊዮን ብር የተቀማጭ ገንዘብ የያዘ ሲሆን፣ ይህም የሁሉም ባንኮች 50.1 በመቶ ድርሻ አለው፡፡

ከግል ባንኮች አቢሲንያ ባንክ እስከ ሚያዝያ ወር ድረስ ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ከወለድ ነጻ አገልግሎት ደንበኞች 41.7 ቢሊዮን ብር ማሰብሰቡን እና አገልግሎቱንም በ970 ቅርንጫፎች በኩል እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular