Homeዜናና ወቅታዊዜናየዓለም አቀፉ የእስልምና ሥልጣኔ ሚዲያ ፎረም በኡዝቤኪስታን ታክሸንት ተከፈተ

የዓለም አቀፉ የእስልምና ሥልጣኔ ሚዲያ ፎረም በኡዝቤኪስታን ታክሸንት ተከፈተ

የዓለም አቀፉ የእስልምና ሥልጣኔ ሚዲያ ፎረም በኡዝቤኪስታን መዲና ታክሸንት “የእስልምና ሥልጣኔ፡ አዲስ ዐይታ – አዳዲስ ግኝቶች” በተሰኘ መሪ ቃል ተከፍቷል፡፡ ማክሰኞ እለት በተከፈተው ፎረም ላይ ከሃምሳ ሀገራት የተውጣጡ 300 ገደማ የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮችና ባለሞያዎች ተሣታፊ ሆነዋል፡፡

ለሦስት ቀናት የሚቆየው ፎረም “የእስልምናን ሥልጣኔ በማስተዋወቅ፣ ቅርሶችን ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ በማቆየት እና እስልምናን ላልተቀበሉ ሕዝቦች መረጃውን በጥንቃቄና በታማኝነት በማድረስ ረገድ” የሚዲያ ሚና ምን መሆን እንዳለበት ይመክራል፡፡

የኡዝቤኪስታን የእስልምና ሥልጣኔ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ፊርደውስ ዓብዱልካሊኮቭ እንደተናገሩት፤ ስለ እስልምና የተሳሳቱ አመለካከቶችንና ግምቶችን ለማረም የሚያስችል ግልጽና ወጥ ፖሊሲ መቅረጽ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፤ ማዕከሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የእስልምናን መልዕክት ለማሠራጨትና ለማንጸባረቅ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

በቀዳሚው ቀን ከተካሄዱ የውይይት መድረኮች መካከል አንደኛው “ታዋቂ ግለሰቦች፡ የእስልምናን ቅርስ ለማተዋወቅ የሚረዱ አዳዲስ የሚዲያ ቅርጾች” የሚል ርእስ ነበረው፡፡
በእነዚህ መድረኮች በሥልጣኔ እና በባሕል የተወራረሱ ቅርሶችን ለዓለም አቀፍ ዕድምተኞች ለማቅረብ እና አዲሱን ትውልድ ለእስልምና ሥልጣኔ አስተዋጽኦ ካደረጉ ሊቃውንት ጋር ለማስተዋወቅ በዘጋቢ ፊልሞች፣ በዲጂታል አማራጮችና በስትራቴጂካዊ ኮሙኒኬሽን አጠቃቀም ላይ ዓለም አቀፍ ተመክሮዎች ቀርበዋል፡፡ ፎረሙ የሣይንስና የእስልምና ሥልጣኔ ታሪክን በማቅረብ ረገድ የሚዲያና የሲኒማ ተመክሮዎችንም ገምግሟል፡፡

ከእነዚህም መካከል ከሁለት ቢሊዮን በላይ ዕይታዎችን ያገኘው የ“1001 ኢንቬንሽንስ” (1001 Inventions) እና “ዊሽፐርስ ኦፍ ዊዝደም” (Whispers of Wisdom) ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡ ከፕሮጀከቶቹ መካከል “1001 ኢንቬንሽንስ” በእስልምና ወርቃማ ዘመን የተመዘገቡ የሣይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የባሕል ስኬቶችን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በማስተዋወቅ ረገድ በርካት ሽልማቶችን ያሸነፈ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት የዚሁ ፕሮጀክት ሁለተኛ ምዕራፍ መጀመሩ የተበሰረ ሲሆን፣ ትኩረቱ የሊቃውንትንና የፈላስፎችን የሕይወት ታሪክ በሲኒማ ማቅረብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በውይይቶቹ ኡዝቤኪስታን ሲልክ ሮድ በመባል የሚጠራውን ምሥራቅ እስያን ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከሰሜን አፍሪካ ጋር የሚያገናኘው ጥንታዊ የየብስ እና የባህር የንግድ መስመር መረብ ላይ፣ በሰመርቀንድ፣ ቡኻራና ኪቫ ከተሞች ታሪካዊ ቅርስ እንዲሁም እንደ አል ኸዋሪዝሚ፣ ኢብን ሲና እና ኡሉግ ቤግ ያሉ ሊቃውንትን አስተዋጽኦ መነሻ በማድረግ የራሷን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ያደረገችው ጥረት ተነስቷል፡፡

በዚህም የቴሌቪዥን፣ የዲጂታል አማራጮች፣ የማኅበራዊ ሚዲያና የፖድካስቶች አጠቃቀም ተዳሷል፡፡ ማሊ ቲምቡክቱን ለማስተዋወቅ ያደረገችው ተመክሮ፣ ጋዜጠኞች ባህላዊ ለውውጦችን በማስተላለፍ በኩል ያላቸው ሚና እንዲሁም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ዲጂታል ምሥል በመፍጠር ሥራዎችን ለአዲሱ ትውልድ ሳቢ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተዳሰዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular