Homeዜናና ወቅታዊዜናአሜሪካ ለኢትዮጵያውያን ሰጥታ የነበረው የጊዜያዊ መጠለያ ፈቃድ የፍርድ ቤት እግድ መነሳቱን ተከትሎ...

አሜሪካ ለኢትዮጵያውያን ሰጥታ የነበረው የጊዜያዊ መጠለያ ፈቃድ የፍርድ ቤት እግድ መነሳቱን ተከትሎ የሀገር ውስጥ ደኅነነት መስሪያ ቤት ስደተኞች ዩናይትድ ስቴትስን ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

አሜሪካ ለኢትዮጵያውያን ሰጥታው የነበረውን የጊዜያዊ መጠለያ ፈቃድ (Temporary Protected Status) ማቋረጥ ለጊዜው እንዳይተገበር የከለከለው የፍርድ ቤት እገዳ መነሳቱን ተከትሎ፣ የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት፤ “ሁሉም ጊዜያዊ ፈቃድ የማቋረጥ ርምጃዎች አሁን በሥራ ላይ ውለዋል፤ ፈቃድ የተሰረዘባቸው ሰዎች አሁን ሊወጡ ይገባል” ሲል በኤክስ ገጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ መሥሪያ ቤቱ ስደተኞች “[በራሳቸው ጊዜ] ካልወጡ እኛ ከሀገር እናባርራቸዋለን” ሲል ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ይህ የመጣው በአሜሪካን ሀገር ቦስተን ውስጥ የሚገኘው የፌዴራል ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከ5 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያንን ከሀገር እንዳያባርር የተጣለውን እግድ ካነሳ በኋላ ነው፡፡ የዩኤስ ዲስትሪክት ዳኛ ብሪያን መርፊ ጊዜያዊ የሕግ ከለላው እንዲያበቃ ውሳኔ ያሳለፉት ነሐሴ 12/2018 ነው፡፡ ከዚህ ውሳኔ በኋላ የሆምላንድ ሴኪዩሪቲ ዋና የሕግ አማካሪ ጄምስ ፐርሲቫል ከአሁን ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሥልጣን ዘመን በ2014 ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለስደተኞች ሰጥቶ የነበረው ሕጋዊ ከለላ፤ በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች በሀገራቸው ያለው ሁኔታ ለመመለስ አስጊ ነው ተብሎ ሲታመን በዚያው እንዲቆዩ እና የሥራ ፈቃድ የሚያመቻች ነው።

ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ2017 ለሁለተኛ የሥራ ዘመናቸው ወደ ሥልጣን ከተመለሱ ወዲህ ይህን ከለላ ለማስቀረት ሲሠሩ ቆይተዋል። ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያውያን ስደተኞችና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች “በሰብአዊ ቀውስና በጦር ግጭት ውስጥ እየታመሰች ነው” ላሏት ሀገራቸው የመባረር እድል ለተጋረጠባቸው በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጥበቃ እንዲደረግ የአስቸኳይ ጊዜ ክስ መስርተው ነበር፡፡  

ክሱን የመሰረቱት አፍሪካን ኮሙኒቲስ ቱጌዘር የተሰኘ የአፍሪካ ስደተኞች ማኅበር እና ሦስት ጊዜያዊ ጥበቃ የተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው። ክሱ የቀረበለት በቦስተን የሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረውን ጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ የሚያቋርጠውን የትራምፕ ትዕዛዝ በጊዜያዊነት አግዶት ነበር፡፡

ዳኛ ብሪያን መርፊ በወቅቱ ባስተላለፉት ውሳኔ፤ የትራምፕ አስተዳደር ጥበቃውን ለማቋረጥ የወሰደው ርምጃ በኮንግረስ የተቀመጠውን ሕጋዊ የአሠራር ሂደት ያልተከተለና “ሕገ ወጥ” ነው ብለውታል። ይህ ውሳኔ በሥራና በመኖሪያ ፈቃድ ላይ ለነበሩት ኢትዮጵያውያን የፍርድ ቤቱ ክርክር እስኪያልቅ ድረስ ከለላው እንዲቀጥል ዕድል ሰጥቶ ነበር።

እስከ ባለፈው መጋቢት ወር ድረስ በአሜሪካ መንግሥት የጊዜያዊ መጠለያ ፈቃድ ጥበቃ ሥር በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር 1 ነጥብ 29 ሚሊዮን ገደማ እንደነበር ተገልጿል፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች የአሜሪካ መንግሥት “ለኑሮ አደገኛ ወይም ያልተረጋገጡ” በሚል የለያቸውን 17 ሀገራት የሚወክሉ ናቸው፡፡ የትራምፕ አስተዳደር ከእነዚህ መካከል የ13ቱን ጥበቃ ለማንሳት ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ የፒው ምርምር ማዕከል ግምት እንደሚያሳየው፣ ይህ ጥበቃ መሻር ውሳኔ እስከዚህ ዓመት ድረስ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የነበሩ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን የሚነካ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular