Homeዜናና ወቅታዊዜናየቴክሳስ አስተዳዳሪ የውዱዕ ማድረጊያ ቦታ በሚያዘጋጁ ኤርፖርቶች ላይ የሰነዘሩት ማስፈራሪያ በአሜሪካ ትልቁ...

የቴክሳስ አስተዳዳሪ የውዱዕ ማድረጊያ ቦታ በሚያዘጋጁ ኤርፖርቶች ላይ የሰነዘሩት ማስፈራሪያ በአሜሪካ ትልቁ የሙስሊሞች መብት ተሟጋች ውግዘት ገጠመው

የአሜሪካ ሙስሊሞች መብት ተሟጋቹ ‘ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ’፤ የቴክሳስ አስተዳዳሪ ግሬት አቦት የውዱዕ ማድረጊያ ቦታ በሚያዘጋጁ የግዛቱ ኤርፖርቶች ላይ የሰነዘሩትን ማስፈራሪያ የሚተች መግለጫ አውጥቷል፡፡ ይህ የካውንስሉ ትችት የመጣው፣ አስተዳዳሪው ቴክሳስ ውስጥ የውዱዕ ማድረጊያ ቦታ ለሚያዘጋጁ ኤርፖርቶች “የበጀት ድጋፍ እናቋርጣለን” የሚል ዛቻ ከሰነዘሩ በኋላ ነው፡፡

ካውንስሉ በኤክስ ገጹ በሰጠው ምላሽ፤ አቦት ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሙስሊሞች ላይ ከፈጠሯቸው ውዝግቦች መካከል፣ የኤርፖርት ውዱዕ ቦታን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት “በጣም አላስፈላጊ እና ግብዝነት የተሞላበት ነው” ሲል ነቅፎታል፡፡

በአሜሪካ በሚገኙ ኤርፖርቶች ከደኅንነት ፍተሻ በፊት ያለውና ለሕዝብ ክፍት የሆነው ክፍል አብዛኛውን ጊዜ በግዛት አስተዳዳሪዎች የሚመራ ሲሆን፣ የበረራ ትኬት ላላቸው ተጓዦች ብቻ ክፍት የሆነው ከደኅንነት ፍተሻ በኋላ ያለው ክፍል ደግሞ በፌዴራል መንግሥት ስር የሚተዳደር ነው፡፡

የዳላስ ፎርት ዎርዝ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ወደ ተጓዦች የደኅንነት ፍተሻ ክፍል ከመግባታቸው በፊት ውዱዕ ለማድረግ የሚጠቀሙበትን ቦታ ለመገንባት በእቅድ ይዞ የነበረውን ፕሮጀክት በወግ አጥባቂው ሪፐብሊካን አስተዳዳሪ ዛቻ ምክንያት ሰርዟል፡፡ 

በግዛቲቱ ውስጥ “ለሙስሊሞች ምቾት ሲባል” የሚከናወኑ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለማስቆም ሲሞክሩ እንደነበርም ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡ ባለፈው ጁምዐ ለአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሾን ዳፊ እና ለአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቶድ ብላንች በላኩት ደብዳቤም የውዱዕ ማድረጊያ ፕሮጀክቱን “ሕገ ወጥ” ነው ብለውታል፡፡ አክለውም የትራምፕ አስተዳደር በሁለቱም የዳላስ እና ሂዩስተን ኤርፖርቶች ለሙስሊሞች የተደረጉ ማናቸውንም ነባር አገልግሎቶች እንዲመረምር ጠይቀዋል፡፡

አስተዳዳሪው ከዚህ ውጭ በአሜሪካ ትልቁ የሙስሊሞች መበት ተሟጋች ነው በሚባለው በ‘ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ’ ላይ ተደጋጋሚ ትችት ከመሰንዘር ባለፈ፣ ድርጅቱን “ሽብርተኛ” ሲሉ ፈርጀውታል፡፡ ካውንስሉ በበኩሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል፡፡ ሰኞ እለት ባወጣው መግለጫም፤ አቦት “የታክስ ከፋዩን ገንዘብ በፀረ ሙስሊም የፖለቲካ ሴራ ላይ ከማባከን ይልቅ፣ በአመራራቸው ስር ባሉ የቴክሳስ እውነተኛ ችግሮች ላይ ማለትም ጉዳት ከሚያደርሱ የመረጃ ማዕከላት እስከ ትምህርት ቤቶች የጦር መሳሪያ ጥቃቶች፣ ከኢኮኖሚ እኩልነት ማጣት እስከ የሃይማኖት ነጻነት መሸርሸር ባሉት ላይ ትኩረት ማድረግ ነበረባቸው” ሲል ተችቷል፡፡

በአሜሪካ የሚገኙ አብዛኞቹ ትላልቅ ኤርፖቶች ተጓዦች ሰላት እንዲሁም ለጥሞና የሚጠቀሟቸው ጸጥታቸው የተጠበቀ የጋራ የሃይማኖች ቦታዎች (interfaith spaces) አላቸው፡፡ የዳላስ ግዛት በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ሙስሊሞችን በስፋት ከያዙ አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular