Homeዜናና ወቅታዊዜናበቁድስ እና መስጂደል አቅሷ ሐሳብ አፍላቂነት የዓለም አቀፍ ቁርኣን ጉባኤ በኢስታንቡል ተመሠረተ

በቁድስ እና መስጂደል አቅሷ ሐሳብ አፍላቂነት የዓለም አቀፍ ቁርኣን ጉባኤ በኢስታንቡል ተመሠረተ

በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ እስላማዊ ማዕከላትን የቁርኣን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው የተባለው ዓለም አቀፍ የቁርኣን ጉባኤ በቱርክ መዲና ኢስታምቡል ይፋ ተደርጓል፡፡ ጉባኤው ይፋ የተደረገው በ11ኛው የኢስታንቡል ዓለም አቀፍ የዐረቢኛ መጻሕፍት ኤግዚቢሽን ላይ ነው። “ታሪኩ ይቀጥላል” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን፣ እስከ ነሐሴ 17/2018 ድረስ ለዘጠኝ ቀናት የሚቀጥል ነው፡፡

ከሙስሊሙ ዓለም የተውጣጡ የሃይማኖት ሊቃውንት፣ የዓለም ቁርኣን ጉባኤ መመሥረቱን ይፋ ያደረጉት በጉባዔው የመጀመርያ ቀን ነሐሴ 9/2018 ነው፡፡ የጉባኤው መሥራች ቦርድ ባወጣው መግለጫ፤ “የዓለም ቁርኣን ጉባኤ መመሥረቱን እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ተቋማት፣ ማዕከላት፣ የቁርኣን ማኅበራት እና የቁርኣን አካዳሚዎች የመመዝገቢያ ፕላትፎርም መከፈቱን እንገልጻለን” ብሏል።

በቁርኣናዊ ተቋማዊ እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ “ወሳኝ ምዕራፍ ነው” የተባለው የጉባኤው ምሥረታ፤ ሐሳቡ የመነጨው ከመስጂደል አቅሷ እና ከቁድስ መሆኑ ተገልጿል።

“በቁርኣን አስተምህሮ የሚመሩ እና አንድ ዐይነት መልእክት የሚያስተላልፉትን ሁሉ በአንድነት ማስተሳሰር” ዓላማ ያደረገው ጉባኤው፤ የተቋቋመው እንደ አንድ ‘የበላይ ተቋም’ ሳይሆን እንደ ዓለም አቀፍ “ጥላ ሆኖ” በአቃፊነት ለማገልገል እንደሆነም ተገልጿል።

የቁርኣን ተቋማትን ማጠናከር፣ ነጻነታቸውን እና ማንነታቸውን የማስጠበቅ እንዲሁም ለትብብርና አጋርነት በር የመክፈት ዕቅድ መያዙም ተመላክቷል። ዓለም አቀፍ የቁርኣን ጉባኤው ቦርድ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የእስልምና ሊቃውንት እና ቃሪኦችን በአባልነት ያቀፈ ነው።

በፕሬዝዳንትነት የተሰየሙት ግብጻዊው የቁርኣን ሊቅ ዶክተር አሕመድ ዒሳ አል መዕስራዊ ሲሆኑ፣ የኳታሩ ዓብዱልረሺድ ሱፊ በምክትልነት ፕሬዝዳንትነት እንዲሁም ዮርዳኖሳዊው አሕመድ ሹክሪ በዋና ጸሐፊነት ያገለግላሉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አሕመድ ዒሳ ከዕውቁ አል አዝሃር ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ድግሪያቸውን ያገኙት በቂርኣት ነው፡፡ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ከቁርኣን በተጨማሪ ሐዲሥ ደርበው አጥንተዋል፡፡ የዶክትሬት ድግሪያቸውንም በሐዲሥ ጥናት አጠናቀዋል፡፡  

ዶክተር አሕመድ ዒሳ አል መዕስራዊ

ዓለም አቀፍ የቁርኣን ጉባኤ ከእነዚህ ሊቃውንት በተጨማሪ፤ ከየመን፣ ቱርክ፣ ኢራቅ፣ አልጄሪያ፣ ፓኪስታን፣ ኮሶቮ፣ ፍልስጤም፣ ኢንዲኔዥያ፣ ሞሮኮ፣ ሶሪያ፣ ኩዌት፣ አሜሪካ እና ጣሊያን ያቀፈ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular