Homeየቲቪ ፕሮግራሞች“ማነው?” በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሥም ደም የሚለግሠው” የተሰኘ ሀገር አቀፍ የደም ልገሣ ዘመቻ...

“ማነው?” በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሥም ደም የሚለግሠው” የተሰኘ ሀገር አቀፍ የደም ልገሣ ዘመቻ ሊካሄድ ነው

በተማሪዎች እና ወጣቶች ላይ የሚንቀሳቀሰው የሙስሊም ተማሪዎች ሊግ፤ በሂጅሪ የዘመን አቆጣጠር በነገው እለት የሚጀምረውን የረቢዕ አል አወል ወርን አስመልክቶ “ማነው” በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሥም ደም የሚለግሠው?” የተሠኘ የደም ልገሣ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ሊያካሄድ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ሙስሊም ተማሪዎች ሊግ ይህን ዘመቻ ይፋ ያደረገው፣ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 7/2018 በሰጠው መግለጫ ነው፡፡

በመግለጫው ላይ እንደተገለጸው፤ የደም ልገሣ ዘመቻው የሚካሄደው ከነሐሴ 21 እስከ 24፤ 2018፤ ከኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጋር በመተባበር ነው። ዘመቻው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞችም የሚካሄድ ነው፡፡

የዘመቻው ፕሮጀክት ማናጀር አቶ አክረም ሙሐመድ፤ የደም ልገሣ ንቅናቄው “በአዲስ አበባ፣ ጅማ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ዲላ እና ሌሎችም አስር ከተሞች” ይከናወናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

የሊጉ የቦርድ አባል አቶ መንሱር ዓብደላ በበኩላቸው፤ ‘እምነት እና ሌሎችንም ማንነቶች ሳይለይ’ ለአራት ቀናት ይቆያል ባሉት የደም ልገሣ ዘመቻ፣ በሺሕዎች ከሚቆጠሩ በጎ ፍቃደኞች አምስት ሺሕ ዩኒት ደም ለማሰገሰብ በእቅድ መቀመጡን አስረድተዋል፡፡ ከደም ልገሣ በተጨማሪ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራም የዘመቻው አካል መሆኑን አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደም እና ሕብረ ህዋስ አገልግሎት የደም ልገሣ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር መላሽ ገላው በበኩላቸው፤ “ደም መለገሥ ሕይወት መለገሥ ነው” ያሉ ሲሆን፣ ለሊጉ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በክረምት መርሐ ግብር 150 ሺሕ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለጹት ዶ/ር መላሽ፣ ሊጉ የጀመረውን ዘመቻ ማስቀጠል እንዳለበት የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሙስሊም ተማሪዎች ሊግ የደም ልገሣ የሚያደርግበት ረቢዕ አል አወል ወር በእስልምና አቆጣጠር ሦስተኛው ወር ነው፡፡ ይህ ወር የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የውልደት፣ የስደት (ሂጅራ) እንዲሁም የኅልፈት ወር ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular