ብራዚል የምትመራው ዓለም አቀፉ የሐላል ምግብ ገበያ፣ በ2029 ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ያመለከተው፤ ለ12ኛ ጊዜ የታተመው “ስቴት ኦፍ ዘ ግሎባል ኢኮኖሚ 2025/2026 ሪፖርት” ነው፡፡
በሪፖርቱ መሠረት፣ የዘርፉ ገበያ እ.አ.አ በ2024 1.53 ትሪሊዮን የነበረ ሲሆን፣ በ2029 ወደ 2.06 ትሪሊዮን ዶላር ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም ለላኪ ሀገራት አዳዲስ ዕድሎችን የሚከፍት ነው፡፡
ለእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል ሀገራት የምትልከውን የምግብ ወጪ ንግድ በግንባር ቀደምነት የምትመራው ብራዚል፣ በ2024 ሀገሪቱ 3.33 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምግብ ለእስላማዊ ትብብር ድርጅት ሀገራት ገበያ አቅርባለች፡፡ ብራዚልን የሚከተሉት ቻይና 32.6 ሚሊዮን ዶላር፣ ሕንድ 28.7 ሚሊዮን ዶላር፣ የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬትስ 21 ሚሊዮን ዶላር እና ቱርክ 18.7 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምግብ ልከዋል፡፡ በብራዚል በተለይም ሐላል ሠርተፍኬት ያላቸው የዶሮ ሥጋ ላኪዎች ወደ ሙስሊሙ ዓለም ገበያ በሥፋት ገብተዋል፡፡
የሐላል ሠርተፍኬት ሒደቱ አጠቃላይ የምርት ሰንሰለቱ ከጥሬ ዕቃ መረጣ እስከ እርድ፣ ማዘጋጀት፣ ማከማቸት እና ማጓጓዝ ድረስ ከእስልምና ሕግጋት ጋር የተጣጣመ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ በእስልምና አስተምህሮ መሠረት የእንስሳት እርድ በሚፈጸምበት ወቅት፣ ለምግብነት “ሐላል” (የተፈቀደ) ለመሆን የተቀመጠውን መሥፈርት እንዲያሟላ ይጠበቃል፡፡ ከመሥፈርቶች ውስጥ ስለት ያለው መሣሪያ መጠቀም፣ ለእርድ የሚቀርበው እንስሳ ጤናማ አቋም ላይ መገኘት እንዲሁም በአላህ (ሱ.ወ) ሥም መታረዱ ይጠቀሳል፡፡
ከሃይማኖቱ እሴት ባሻገር፣ የሐላል ሠርተፍኬት የጥራት፣ የታማኝነት እና የምግብ ምልክት ተደርጎ እየተወሰደ እንደሚገኝ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እነዚህ እሴቶች ሙስሊም ባልሆኑ ደንበኞች ዘንድም ከፍተኛ ግምት ይሰጣቸዋል፡፡
የሐላል ምግብ አቅርቦት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ የሚገኘው ሐላል ኢንዱስትሪ አንደኛው ዘርፍ ነው፡፡ ሰባት ዘርፎችን የሚያቅፈው ይህ ኢንዱስትሪ፤ በሥሩ እስላማዊ ፋይናንስ፣ ሐላል ቱሪዝም፣ ሐላል ፋሽን፣ ሐላል ሚዲያ እና መዝናኛ፣ የመድኃኒት እና ሐላል መዋቢያዎችን የሚያካትት ነው። (ሚንበር ቲቪ)












