የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቶ ዓብዱልጁሃድ ሐሰን ሙሐመድን ሸሪዓን መስእረት ያደረገ አገልግሎት የሚሰጠው የሸበሌ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሹመት በይፋ አጽድቋል። ይህም ባንኩ የትርፍ መጠኑን በዐሥር እጥፍ ባሳደገበት እና የሐብት መጠኑን በእጥፍ በጨመረበት የዘጠኝ ወራት የጊዚያዊ ሥራ አስፈፃሚነት ጊዜ ማጠቃለያ ሆኗል።
ብሔራዊ ባንክ ደንብ፣ ፈቃድና አፅዳቂ ዳይሬክቶሬት ሹመቱን ነሐሴ 1/2018 ያፀደቀው፣ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጥያቄውን ባቀረበ በሦስተኛው ቀን ነው።
አዲሱ ተሿሚ ዓብዱልጁሃድ ሐሰን በባንክ ዘርፍ የ17 ዓመታት የባንክ ሥራ ልምድ አላቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ለ11 ዓመት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በሚገኙ አምስት ተቋማት ውስጥ በአመራር ደረጃ አገልግለዋል። የባንክ ሞያቸውን በ2001 በወጋገን ባንክ በግል ባንከርነት የጀመሩት ዓብዱልመጂድ፣ በመቀጠል ወደ ሕብረት ባንክ በመዛወር ብድርና የውጭ ንግድ ፋይናንስ ኦፊሰር፣ በኋላም ወደ ኦሮሚያ ባንክ በመሸጋገር ለአምስት ዓመታት የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል።
በ2013 ሌላኛውን ከወለድ ነጻ አገልግሎት ሰጪ ዘምዘም ባንክን የተቀላቀሉት ዓብዱልጁሃድ፣ በቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅነት፣ በዲጂታል አገልግሎቶች፤ በመጨረሻም የኮርፖሬት ባንኪንግ እና የደንበኞች ግንኙነት አስተዳደር ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። በመቀጠልም በሐምሌ ወር 2017 የሸበሌ ባንክ የባንኪንግ እና ማይክሮፋይናንስ ኦፕሬሽንስ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተቀላቅለዋል። ከዚያም ከአራት ወራት በኋላ በኅዳር ወር 2018 ወደ ጊዚያዊ ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ማደጋቸው ተገልጿል።
ይህ ሹመት የመጣው ሸበሌ ባንክ በንግድ እና ፋይናንስ አፈፃፀሙ ላይ ከፍተኛ እድገት በማስመዝገብ እና ወደ አዲሱ የበጀት ዓመት በገባበት ወቅት ነው። ባንኩ ከታክስ በፊት ያለው የትርፍ መጠን በ2018 የበጀት ዓመት በዐሥር እጥፍ በማደግ 231 ሚሊዮን ብር ደርሷል።
ባንኩ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት የደንበኞች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ122 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ ሲያድግ፣ የባንኩ ጠቅላላ ኢንቨስትመንትም እንዲሁ በ101 በመቶ በማደግ 3.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
በተጨማሪም የባንኩ ጠቅላላ ሐብት በአሁኑ ወቅት 9.7 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም የ55 በመቶ ዕድገት በማሳየት የንግድ ሥራው መስፋፋቱን እና የደንበኞችን አመኔታ መጠናከሩን የሚያንፀባርቅ ሆኗል ተብሏል። (ሚንበር ቲቪ)












