Homeዜናና ወቅታዊዜናበፈረንሣይ የቁርኣን አንቀጽ እና እንደ “ሪያዱ አስ ሷሊሒን” ያሉ ታዋቂ የእስልምና ኪታቦችን...

በፈረንሣይ የቁርኣን አንቀጽ እና እንደ “ሪያዱ አስ ሷሊሒን” ያሉ ታዋቂ የእስልምና ኪታቦችን በመጥቀስ ዳዕዋ የተደረገበት መስጂድ መዘጋቱ በሀገሪቱ “የሃይማኖት ነጻነት” ላይ አዲስ ሥጋት ደቅኗል

የፈረንሣይ ፍርድ ቤት በፓሪስ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የሻንተሉፕ መስጂድ ለስድስት ወራት ተዘግቶ እንዲቆይ የተሰጠውን ውሳኔ ማጽናቱ፣ መንግሥት በእስልምና ሃይማኖት እና እሴቶች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር በተመለከተ አዲስ ሥጋት ደቅኗል፡፡ የሞንትሬይ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ያጸናው፣ የሻንተሉፕ መስጂድ በሐምሌ ወር የተላለፈውን ውሳኔ ለማንሳት ባቀረበው አቤቱታ ላይ በሰጠው ብይን ላይ ነው፡፡ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት፣ መስጂዱ እስከ ቀጣይ ዓመት ጥር ወር ድረስ ተዝግቶ ይቆያል፡፡

መስጂዱን ወክለው የሚከራከሩት የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ረፊቅ ቼካት፣ “ተገርመንበታል” ካሉት ውሳኔ በኋላ በሀገሪቱ የሚገኙ ኢማሞች የቅዱስ ቁርኣንን የመስበክ ነጻነታቸው “አሁንም ተጠብቆ አለ ወይ?” የሚል ጥያቄ መሰንዘራቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል፡፡  

ጠበቃው በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደገለጹት፣ ባለሥልጣናት ለውሳኔያቸው መነሻ ያደረጉት ኢማሞች “ከቁርኣን ሰባት አንቀጾችን እንዲሁም በኢማም አን ነወዊ ከተሰናዳው “ሪያዱ አስ ሷሊሒን” ኪታብ መጥቀሳቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ኢማሞች ዳዕዋ በሚያቀርቡበት ጊዜ በሌሎች ቤተ እምነቶች ስብከት ውስጥም በተመሳሳይ የሚጠቀሰው “ስለ ጀሐነም” እና “እምነት የለሽ” ሰዎች ስለተዘጋጀው ቅጣት መናገራቸውን ነው፡፡

የሰይን ሴንት ደኒ ግዛት አስተዳዳሪ ዡሊየስ ቻርለስ ውሳኔውን ባሳለፉበት ወቅት፤ ባለሥልጣናቱ መስጂዱን ሲዘጉ “በሃይማኖቱ የመመለክ ነጻነት ላይ በግልጽ የታየ ከፍተኛ የሚባል ሕገ ወጥ ጥሰት አልፈጸሙም” ብለዋል፡፡

ብይኑን የተቃወሙት የመስጂዱ ጠበቃ ረፊቅ ቼካት በበኩላቸው፤ የውሳኔው የተወሰኑ ክፍሎች “ከሃይማኖት ነጻነት ጋር ሙሉ ለሙሉ የሚጋጩ” መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ አክለውም “ዳኛው የግዛቱን አስተዳዳሪ ሐሳብ መቃወም እንዳለፈለገ እረዳለሁ፤ አሁን ግን በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተሻለ ዕድል ይኖረናል፤ ውሳኔውም ከፖለቲካ ይልቅ ሕጋዊነቱ ያመዝናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል፡፡

ውሳኔውን በመቃወምና “የሃይማኖት ነጻነትን እና የመንግሥት እና ሃይማኖት መለየት” መርሕን ለማስከበር ይግባኝ የሚሉት በከፍተኛው የአስተዳደር ፍርድ ቤት ነው፡፡

ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ ይህ ውሳኔ የተሰጠው የፈረንሣይ መንግሥት በሙስሊም ተቋማት ላይ የሚያደርገውን ጫና እያሰፋ ባለበት ወቅት ነው፡፡ የፈረንሣይ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም እ18 ወራት ብቻ ምንጫቸው ያለተገለጸ የመረጃ ሰነዶችን በመጠቀም 22 መስጂዶችን ዘግተዋል፡፡ ይህም ፈረንሣይ የደኅነት ሕጎችን ተጠቅማ የሙስሊሞችን የእምነት ነጻነት እያጠበበች ነው የሚለውን ሥጋት አጠናክሮታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular