በአፍሪካ አሕጉር የሚገኙ ፍልሰተኛ ሠራተኞች ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2010 ከነበረበት 9.3 ሚሊዮን ተነስቶ፤ 13.1 ሚሊዮን ደርሷል መድረሱን የአፍሪካ ኅብረት ይፋ ባደረገው ሪፖርት አመልክቷል። ከእነዚህ ሠራተኞች መካከል ሴቶች 37 በመቶውን ሲሸፍኑ፣ የወንዶች ቁጥር ደግሞ 63 በመቶ ነው፡፡
መረጃው ለሕዝብ የተለቀቀው በቅርቡ ይፋ በተደረገው “በአፍሪካ ፍልሰተኛ ሠራተኞች ስታቲስቲክስ ሪፖርት 4ኛ ዕትም” ላይ ነው፡፡ ሪፖርቱ የመዘገበው “የትውልድ ወይም የዜግነት ሀገራቸውን ለቀው በሌላ የአፍሪካ ሀገር ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ላይ የተሰማሩ” ሰዎችን አሕዝ ነው፡፡ ይኸው ሪፖርት በናሚቢያ ዊንድሁክ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የማኅበራዊ ልማት፣ የሠራተኛና የሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ስድስተኛው መደበኛ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ይፋ ተደርጓል፡፡
በሪፖርቱ መሠረት፤ በአፍሪካ ከሚገኙ 26 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ፍልሰተኞች መካከል 20.4 ሚሊዮኑ ለሥራ የደረሱ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ በሥራ ላይ ያሉት 64 በመቶ ናቸው፡፡ ከሀገሮች መካከል በምዕራብ እና ምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙት 48 በመቶ ዓለም አቀፍ ፍልሰተኛ ሠራተኞችን ያስተናግዳሉ። ምዕራብ፣ ምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ በጣምራ ደግሞ 78 በመቶ ፍልሰተኛ ሠራተኞችን አቅፈዋል፡፡
የጾታ ልዩነት በቀጣናዎች መካከል በእጅጉ ይለያያል፡፡ በእያንዳንዱ የቀጣና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ውስጥ በሚሠሩ ፍልሰተኛ ሠራተኞች ቁጥር ላይ ወንዶች አብላጫውን ሲይዙ፣ ከፍተኛ ልዩነት የሚታየው በዓረብ መግሪብ ኅብረት ውስጥ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ 78 በመቶ የሚሆኑት ፍልሰተኛ ሠራተኞች ወንዶች ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 35 የሆኑ ወጣት ፍልሰተኛ ሠራተኞች ቁጥር 6.1 ሚሊዮን ነው፡፡ ወንዶቹ የዚህን 60 በመቶ ገደማ ይሸፍናሉ፡፡
ወደ አፍሪካ የሚላከው የገንዘብ መጠን መጨመሩን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ እ.ኤ.አ. በ2013 ከነበረበት 64.8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ 97.5 ቢሊዮን ዶላር ማደጉን ያሳያል። ከዚህ ውስጥ ሰሜን አፍሪካ 45 በመቶ፣ ምዕራብ አፍሪካ ደግሞ 34 በመቶ ያህሉን ይቀበላሉ ብሏል።
በሪፖርቱ ይፋ ማድረጊያ ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙት የአፍሪካ ኅብረት የጤና፣ ሰብአዊ ጉዳዮች እና ማኅበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር አማ ኤ. ቱውም አሞአ እንደተናገሩት፤ ወቅታዊና አስተማማኝ የመረጃ አሰባሰብ ለአህጉሪቱ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። አክለውም “በበቂ ሁኔታ ልንለካው የማንችለውን ጉዳይ በትክክል ማስተዳደር አንችልም” ሲሉ ገልጸዋል።
የደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የበላይ ኃላፊና የደቡባዊ አፍሪካ ንዑስ ቀጣና ዳይሬክተር ይጥና ጌታቸው፤ “ቀጣዩ ጊዜ በዲጂታል አስተዳደር ሥርዐቶች፣ እርስ በርስ በሚገናኙ የመረጃ ቋቶች እና በተቋማት አቅም ላይ በዘላቂነት ኢንቨስት ማድረግ ይጠይቃል” ብለዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












