Homeዜናና ወቅታዊዜናኢትዮጵያ ለዲጂታል ጥቃት ተጋላጭ ከሆኑ የአፍሪካ ሀገሮች አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠች

ኢትዮጵያ ለዲጂታል ጥቃት ተጋላጭ ከሆኑ የአፍሪካ ሀገሮች አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠች

ኢንተርፖል አዲስ ባወጣው የሳይበር ሥጋት ግምገማ ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ጥቃት ተጋላጭነት እ.አ.አ በ2025 ከአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ኢትዮጵያ በአሕጉሩ በዓመቱ ውስጥ ከተመዘገቡት የዲጂታል ጥቃት ተጋላጭነቶች 3.3 በመቶ የሚሆነው ተመዝግቦባታል፡፡ ለዚህ ተጋላጭ ያደረጋት “ፈጣን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞዋ ከሳይበር ደኅንነት መከላከያ እና ተቋማዊ ዝግጁነት ጋር አለመጣጣሙ” እንደሆነ ተገልጿል።

በአፍሪካ ውስጥ የተፈፀመው የሳይበር ወንጀል ከ55 በመቶ በላይ የሚሆነው ከሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ) ጋር የተገናኘ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በሪፖርቱ መሠረት፤ በአፍሪካ የሳይበር ወንጀል ያስከተለው ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሲደርስ፣ ለሳይበር ደኅንነት የወጣው ወጪ ደግሞ 15.3 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ የተመዘገበው የገንዘብ ኪሳራ ከ192 ሚሊዮን ዶላር ወደ 484 ሚሊዮን ዶላር ከእጥፍ በላይ አድጓል፡፡ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ አካላት ቁጥር ደግሞ ከ35 ሺሕ ወደ 87 ሺሕ አሻቅቧል፡፡

በዓለም ደረጃ በሳይበር አጥቂዎች ተጠልፈው (በቫይረስ ተበክለው) የአጥቂዎቹ መረብ (ቦትኔት) አካል ከሆኑት በኢንተርኔት ከተገናኙ መሣሪያዎች መካከል 1.36 በመቶ የሚገኙት በኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚታገዝ የዲጂታል ማጭበርበር ድርጊቶችም እያደገ የመጣ ማኅበራዊ ስጋት ሆኗል፡፡ ያልዘመኑ ሶፍትዌሮች፣ የኦንላይን እንቅስቃሴ፣ መረጃ እና ማንነት ከሌሎች አካላት ለመሰወር ጥቅም ላይ የሚውሉ ክፍት “ቪፒኤኖች” እና በአግባቡ ያልተዋቀሩ የሰነድ አስተዳደር ሲስተሞች ዋና ዋና የጥቃት መንስዔዎች ተብለው ተለይተዋል፡፡

ኢንተርፖል በ2025 በአፍሪካ 1.1 ቢሊዮን በላይ የሞባይል ተጠቃሚዎች መኖራቸውንና የአፍሪካ የዲጂታል ዘርፍ በተመሳሳይ እያደገ መምጣቱን ቢገልጽም፤ የሳይበር ወንጀል ሕጎች ወጥ አለመሆናቸውንና የሕግ አስፈጻሚ አካላት ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ያላቸው ዝግጁነት በጣም ዝቅተኛ መሆኑን በድክመት አንስቷል፡፡ ይህ ሁኔታ የገንዘብ ማጭበርበርን ለመዋጋት ክፍተቶችን መፍጠሩ በሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል። የሞባይል ገንዘብ ማጭበርበር በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱን የገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ 97 በመቶ የሚሆኑት ሀገሮች ሪፖርት አድርገዋል ብሏል።

በሪፖርቱ የተጠቀሰው ሌላኛው ጉዳይ “ዲጂታል ሴክስቶርሽን” በመባል የሚጠራው የእርቃን ገላ ፎቶግራፍ በመጠቀም የሚደረግ ዲጂታል ዛቻ እና ማታለል ነው፡፡ በአህጉሩ 600 ሺሕ ጥቃቶች በተመዘገቡበት በዚህ ጥቃት፣ ኢትዮጵያ 8 በመቶ ትሸፍናለች፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሜታ ኩባንያ በ2025 ከኢንስታግራም እና ፌስቡክ 635 ሺሕ አካውንቶችን ማስወገዱ በሪፖርቱ ተገልጿል።

በሪፖርቱ ውስጥ ኢንተርፖል ደረጃውን የጠበቀ ዲጂታል የፎረንሲክ አቅም፣ የድንበር ተሻጋሪ ትብብር ማጠናከር፣ በሕግ አስፈጻሚ አካላት መካከል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዕውቀት ላይ ኢንቨስት ማድረግና ውጤታማ መከላከል፣ መለየት እና ምላሽ መስጠትን ለመደገፍ መደበኛ የመንግሥትና የግል ዘርፍ ጥምረቶች እንዲፈጠሩ ጥሪ አቅርቧል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular