Homeዜናና ወቅታዊዜናየንግድ ደረሰኝ ማጭበርበር ኢትዮጵያን በዐስር ዓመት ውስጥ 24 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር...

የንግድ ደረሰኝ ማጭበርበር ኢትዮጵያን በዐስር ዓመት ውስጥ 24 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር አሳጥቷል – የአፍሪካ ልማት ባንክ

ኢትዮጵያ ከ2005 እስከ 2014 ባሉት አስር ዓመታት ውስጥ በንግድ ደረሰኝ ማጭበርበር በግምት 24 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማጣቷን የአፍሪካ ልማት ባንክ አዲስ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ይፋ ባደረገው “የምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ሁኔታ 2026” ሪፖርት፤ ሕገ ወጥ የፋይናንስ ፍሰቱ ሀገሪቱ ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እና ለሰፊ የመሠረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ የፋይናንስ ፍላጎት በነበራት ወቅት የሀገር ውስጥ ሐብትን በከፍተኛ ደረጃ ሲያመክን የቆየ መሆኑ ተጠቅሷል።

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ እድገቷን ለማስቀጠል እና የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንቶችን ለመደገፍ እስከ 2022 ድረስ በየዓመቱ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ (GDP) ከ11 እስከ 15 በመቶ የሚደርስ ተጨማሪ ፋይናንስ ያስፈልጋታል።

ምሥራቅ አፍሪካ በየዓመቱ የ119 ቢሊዮን ዶላር የልማት ፋይናንስ ክፍተት እንዳለበት የጠቆመው የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ሀገራት ታክስ አስተዳደርን በማሻሻል፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ፍሰትን በመቆጣጠር እና ከግል ዘርፉ ጋር ጥምረት በመፍጠር ተጨማሪ ሐብት ማሰባሰብ እንዳለባቸው አሳስቧል።

የልማት ባንኩ የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ የጉምሩክ አስተዳደርን ማጠናከር፣ ዲጂታል የታክስ ስርዓቶችን ማስፋፋት እና ለንግድ ማጭበርበር ክፍተት የሚፈጥሩ አሠራሮችን መዝጋት አስፈላጊ መሆኑንም አክሏል።

የፋይናንስ ጉድለት ግኝቱ የመጣው ኢትዮጵያ በ2016 ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት መተግበሯን ተከተሎ ቢሆንም በወቅቱ በነበረው የብር ዋጋ መቀነስ የውጭ ዕዳ መጠን እንዲጨምር አድርጓል ሲል ሪፖርቱ አክሏል። በዚህም የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የነበረው ድርሻ በ2016  ከነበረበት 23.8 በመቶ በ2017 ወደ 33.9 በመቶ አድጓል።

ምንም እንኳን የውጭ ምንዛሬ እና የዕዳ ጫና ቢኖርም፣ በ2016 በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ከመጣው 12.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ድርሻ ትይዛለች ብሏል።

ሪፖርቱ አክሎም የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የንግድ ፍሰት 90 በመቶ በላይ በጅቡቲ ወደብ እና በቀይ ባህር ማለፉ ሀገሪቱን ለጂኦፖለቲካዊ ሥጋቶች ተጋላጭ አድርጓታል ሲል አትቷል። በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ግጭት እና በቀይ ባህር የመርከቦች እንቅስቃሴ መስተጓጎል የመርከብ የጭነት ታሪፍ ከ30 በመቶ እስከ 50 በመቶ እንዲጨምር እና የጦርነት ስጋት ኢንሹራንስ ዋጋ እንዲያሻቅብ ማድረጉን ጠቅሷል።

ይህም ኢትዮጵያ እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ እና የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ የምታስገባ በመሆኗ፣ የትራንስፖርት ወጪ መጨመር ለገቢ ዕቃዎች ዋጋ ንረት ምክንያት መሆኑን አካትቷል።

ሪፖርቱ ምሥራቅ አፍሪካ በ2017 የ6.6 በመቶ እውነተኛ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት በማስመዝገብ የቀጣናው ፈጣን እድገት መቀጠሉን ገልጿል። ሆኖም የኢኮኖሚ እድገቱ በ2018 ወደ 5.9 በመቶ ዝቅ እንደሚል እና በቀጣይ ዓመት ደግሞ ወደ 6.4 በመቶ እንደሚያገግም የባንኩ ሪፖርት ገልጻል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular