ናይጄሪያዊው ባለጠጋ አሊኮ ዳንጎቴ፤ ካከማቹት ሐብት አንድ ሦስተኛውን ለበጎ አድራጎት ለማዋል ማቀዳቸውን ልጃቸው ሐሊማ ዳንጎቴ ተናግራለች፡፡ የአሊኮ ዳንጎቴ ፋውንዴሽን አባሏ ሐሊማ ለብሉምበርግ በሰጠችው ቃል ምልልስ፤ ለአባቷ “በጣም አፈላጊ” ያለችው ይህ ስምምነት በሸሪዓ የውርስ ሕግ ተመርኩዞ መዘጋጀቱን አስረድታለች፡፡ ሐሊማ ሐብቱን ለበጎ አድራጎት ከመለገሥ ጋር አያይዛ ባነሳችው ሐሳብ፤ “መስጠት ለንግዳችን ስኬታማነት መሠረት ነው” ስትል ተደምጣለች፡፡
በብሉምበርግ የቢሊዮነሮች ማውጫ መሠረት፤ የአሊኮ ዳንጎቴ የሐብት መጠን 35 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ በዚህ ሥሌት አሁን ለበጎ አድራጎት የሚሰጡት የገንዘብ መጠን 11 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡
ሐሊማ እንደተናገረችው፤ ባለጠጋው አባቷ ይህን ያክል የገንዘብ መጠን ለበጎ አድራጎት ለመስጠት እርሷን ጨምሮ ሁለት ልጆቻቸውን እንዲሁም ወላጅ እናታቸውን የኑዛዜ ሠነድ እንዲፈርሙላቸው ጥያቄ አቅርበውላቸዋል፡፡ አክላም አባቷ “ስኬታማ መሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው” ማድረግ ያለበት ሁለት ነገሮች እንዳሉ ያምናሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች “ለበጎ አድራጎት መለገሥ እና እናትን ማክበር” ናቸው፤ “እርሱ ከማንኛውም ሰው በላይ እናትን ማክበር ላይ አጽንኦት ይሰጣል” ብላለች፡፡
አሊኮ ዳንጎቴ በአሁኑ ሰዓት እድሜያቸው 69 ደርሷል፡፡ በኢኮኖሚ አቅም ደረጃ “ከፍተኛ” ከሚባል ቤተሰብ የተወለዱት ዳንጎቴ፤ ከዚህ ቀደም በበርካታ የበጎ አድራጎት ሥራ ይታወቃሉ፡፡ በተመሳሳይ ወላጅ እናታቸው ማሪያ ዳንታታም በንግድ እና በበጎ አድራጎት ተግባር ላይ በመሳተፍ ሥማቸው ይጠራል፡፡ ባለጠጋው ዳንጎቴ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በመድረሳ ሲሆን፤ እ.አ.አ በ1978 በመንግግስት ኮሌጅ ሁለተኛ ደረጃ ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ግብጽ በመጓዝ በዕውቁ የእስልምና ማዕከል አል አዝሐር ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ስተዲስ ኤንድ አድሚንስትሬሽን የመጀመርያ ድግሪ አጠናቀዋል፡፡
የኢስላም ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት፤ በቁርኣን እና ሐዲስ ላይ የተመሠረተው የውርስ ሕግ፣ የቤተሰብ አባላትን ለመደገፍ እንዲሁም የግለሰብ መብቶችንና ማኅበራዊ ግዴታዎችን ለማክበር ያለመ ነው፡፡ እነዚህ ሕጎች ኢስላም ለቤተሰብ፣ ለማኅበራዊ ኃላፊነት እና ማኅበራዊ ፍትሕ የሚሰጠውን ሥፍራ የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡ ቁርኣን በውርስ ረገድ የአላህ (ሱ.ወ)ን መመርያዎች መከተል ያለውን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲሁ ሐብት በእስልምና ሕግ መሠረት በፍትሐዊነት መከፋፈሉን ማረጋገጥ እና ለውርስ ዝግጅት ማድረግ ያለውን ቦታ አጉልተው አሳይተዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












