Homeዜናና ወቅታዊዜናኢትዮጵያውያን በእስያ የሚገኙ የሳይበር አጭበርባሪዎች ተጠቂ ናቸው - የተመድ

ኢትዮጵያውያን በእስያ የሚገኙ የሳይበር አጭበርባሪዎች ተጠቂ ናቸው – የተመድ

ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን ሥራ ፈላጊዎች በእስያ ሀገሮች ውስጥ በስፋት የሚገኙ የማጭበርበሪያ ካምፖች ተጠቂ መሆናቸው በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት አስጠነቅቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልሰተኞች ኤጀንሲ (አይኦኤም) የወንጀል መረቦች ከሀገር ውጪ ሥራ የሚፈልጉ ሰዎችን በመመልመል፣ ጥብቅ ጥበቃ በሚደረግላቸው ካምፖች ውስጥ አስገብቶ በማስፈራራት፣ ድብደባ እና ስቃይ በመፈጸም የሳይበር ማጭበርበር ይፈጽማሉ ብሏል።

ሐምሌ 23/2018 ከሚከበረው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከያ ዓለም አቀፍ ቀን ዋዜማ አይኦኤም ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ በመላው እስያ ከሚገኙ የማጭበርበሪያ ማዕከላት እንዲወጡ ከተደረጉ ሰዎች መካከል ከምሥራቅ አፍሪካ የተነሱት ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።

የዘንድሮውን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ቀን ነገ ሐሙስ “የማታለል ሰለባዎች” በሚል መሪ ቃል የሚያከብረው ድርጅቱ፤ እ.አ.አ ከ2022 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ኤጀንሲው በደቡብ ምሥራቅ እስያ ለግዳጅ ወንጀል ተግባር ከተወሰዱት ከ39 ሀገሮች ለመጡ ከ3,500 በላይ ሰዎች ድጋፍ አድርጓል። ከእነዚህ መካከል ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከሕንድ፣ ከስሪላንካ፣ ከባንግላዴሽ የመጡ ተጎጂዎች ይገኙበታል።

ዓድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በወንጀል ቡድኖች አማካኝነት የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ በመሆን በቢሊዮን ዶላሮች በሚቆጠር የኢንተርኔት የማታለል ወንጀል ላይ በግዳጅ እንዲሳተፉ እየተደረጉ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ ሁኔታውን አዲስ ብቅ ያለ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መንገድ ነው ሲል የገለጸው ሲሆን፤ ተጎጂዎች ብዙውን ጊዜ በውጭ አገር ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎችን እንደሚያገኙ በሚገልጹ ማስታወቂያዎች አማካኝነት ይሳባሉ ብሏል። ይሁን እንጂ ወደታለመላቸው ሥፍራ ሲደርሱ ፓስፖርታቸውን እንደሚነጠቁና በቋሚ ክትትል ስር ሆነው በኦንላይን የማጭበርበር ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ እንደሚገደዱ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገለጸው አንዳንድ ከካምፖቹ እንዲወጡ የተደረጉ ሰዎች በማጭበርበር ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ድብደባ፣ ፆታዊ ጥቃት እንደተፈጸምባቸው፣ ለረሃብ መዳረጋቸውንና ለብቻ መታሰራቸውን መናገራቸውንም አመልክቷል።

የአይኦኤም የምሥራቅ፣ የአፍሪካ ቀንድ እና የደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ፍራንትዝ ሴሌስቲን፤ በአሁኑ ወቅት በካምቦዲያ፣ ላኦስ እና ምያንማር በሚገኙ ሕገ-ወጥ የጥሪ ማዕከል ኔትወርክ ውስጥ ወደ 300,000 ገደማ ሰዎች ተይዘዋል ብለዋል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የአደንዛዥ ዕፅ እና የወንጀል ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ከሆነ፣ በምሥራቅ እስያ፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ የሚከናወኑ የኦንላይን የማጭበርበር ተግባራት ባለፈው ዓመት ብቻ ከ88 እስከ 114 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ገቢ አስገኝተዋል።

እንዲሁም ለሕገወጥ ሰው ዝውውር የተዳረጉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች በእነዚህ የማጭበርበር ማዕከላት ውስጥ ታጉረው እንደሚገኙ ይታመናል። እንደ ምያንማር፣ ካምቦዲያ እና ላኦስ ባሉ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት የተስፋፉት እነዚህ ካምፖች በየዓመቱ “በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ የሚገኝባቸው” የኦንላይን ማጭበርበሪያ ናቸው።

ሕገ ወጥ የሰዎች እና ሕጻናት ዝውውር፣ የግዳጅ ወንጀለኝነት፣ የሰዎች ስቃይ፣ ሕገ ወጥ ቁማር እንዲሁም በወንጀል የተገኘን ሀብትን ሕጋዊ ማስመሰል የእነዚህ ካምፖች መገለጫ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒት እና የወንጀል ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተገናኘ ባለፈው ሣምንት ከ60 ሰዎች በላይ ለኅልፈት የዳረጉ እና ከ40 ሺሕ በላይ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ያዘዋወሩ 17 አደገኛ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል።
ፌዴራል ፖሊስ እንደገለጸው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የተደራጁ እና በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል በጂቡቲ እና የመን አድርገው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ሲልኩ የቆዩና ከተጎጂዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተቀበሉ ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular