ዶክተር ፋጢማ አልዛህራ ዲቲ ትባላለች፤ የፊሊፒንስ ዜጋ ነች፡፡ አሁን ዕድሜዋ 33 ዓመት ደርሷል፡፡ እነ ፋጢማ ቤት ውስጥ እርሷና እናቷን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አባቷ ከምድር ሕይወት የተለዩት ከዘጠኝ አመት በፊት ነው፡፡ የአምስት ልጆች ታላቅ የሆነችው ዲቲ፤ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነቱ በርሷ ላይ የወደቀ ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ከአባቷ ኅልፈት በኋላም ሆነ በፊት በነበሩት ጊዜያት ወላጆቿ እነሱን ለማሳደግ ሲታገሉ እያየች ስላደገች፣ በቻለችው ሁሉ “ምርጡን የመስጠት” ፍላጎት አድሮባት እሕትና ወንድሞቿን ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ማገዝ ችላለች። “አባቴ ከምድር ሕይወት ሲለይ የቤተሰቡ ኪስ በድንገት ኦና ሆነ፤ እኔም ያንን ሚና መረከብ ነበረብኝ” ትላለች ለዐረብ ኒውስ ጋዜጠኞች፡፡
ዲቲ ይህን የሕይወት መንገዷን ከ2013 ጀምሮ “ዶክ ኩሎት” በሚለው ሥም በቲክቶክ ላይ እያጋራች ቆይታለች፡፡ በርግጥ ስለ ሰፊው ሕይወቷ ከመናገሯ በፊት መጀመርያ ላይ የምታጋራው የሕክምና ተማሪ ስለነበረች የሐኪምነት ልምምድ ጊዜዋን ነበር፡፡ በጊዜ ሒደት የግል ታሪኳን በስፋት ማካፈል ጀመረች፡፡ በታዊ-ታዊ በምትገኝ ሲሙኑል በምትባል ትንሽ ከተማ ማደጓን፣ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሕክምና ትምህርት ቤት ድረስ በነፃ የትምህርት ዕድል መማሯንና በ2009 አባቷ ከሞቱ በኋላ የቤተሰቧ ዋነኛ ገቢ አምጪ መሆኗን ጭምር ለማጋራት ወደ ኋላ አላለችም፡፡
ስለ ሁኔታው ስታስታውስ፦ “ሐኪም እና የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆን የጀመርኩትን ጉዞ ማጋራት ጀመርኩ፤ ሰዎችም ከእኔ ጋር እንዲቀራረቡ ያደረጋቸው ያ ነበር” ትላለች። ይህ ግልጽነቷ “ኩሎቲዝም” የተባለ ታማኝ ተከታይ እንዲኖራት ሲያደርግ፤ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋኗንም በፍጥነት እንዲያድግ አግዟታል፡፡
ለቤተሰቧ “ምርጡን ለመስጠት” የምታትረው ፋጢማ፤ ቤተሰቡን ከመደገፍ ጎን ለጎን አንድ ትልቅ ዓላማ ነበራት፡፡ ይህ ሕልም እናቷን ሐጅ ማስደረግ ነው፡፡ ይህንኑ ለእናትዬው በአንደበቷ ተናግራለች፡፡ ቃል ኪዳን ስትገባ ከልቧ ከማመኗ ውጪ እንዴት እንደምታሳካው አታውቅም ነበር። የጉዞው ወጪ 350 ሺሕ ፔሶ ነው፤ ይህ ደግሞ ገና የትምህርት እዳዋን እየከፈለች ላለችና መላው ቤተሰቧን በአንድ ገቢ ለምታስተዳድር ሐኪም የሚታሰብ አይደለም፡፡
በአንደኛው ቀን ግን ይህን ሕልሟን ለተከታታዮች አጋራች፡፡ እራሷ ስለሁኔታው ስታስታውስ፦ “በአንዱ የቀጥታ ሥርጭቴ ላይ ታሪኬን ሳካፍል መጨረሻ ላይ አለቀስኩ። ያስለቀሰኝ ለእናቴ ይህን ማድረግ ከልቤ የምፈልገው ጉዳይ ስለሆነ ነው፤ ነገር ግን ገንዘቡ በጣም ውድ ነው። ቢሆንም ግን ማሳካት አለብኝ በሚል ነው’ ትላለች፡፡
ይህን የሰሙት የቲክቶክ ተከታዮች በዝምታ የሚያልፉት ጉዳይ አለነበረም፡፡ ስለ ፋይናንስ ሥጋቷ በግልጽ በምትናገርበት የቀጥታ ሥርጭት ወቅት፣ አንድ ተከታይ የፕላትፎርሙን የቀጥታ ሽያጭ እንድትሞክረው ሐሳብ አቀረበላት፤ እርሷም ሐሳቡን ለመተግበር አላመነታችም፡፡ በየቀኑ ሕክምና ስፔሻሊስትነት ፈረቃዋን እንደጨረሰች፣ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት ድረስ ሳሙና እየሸጠች የቀጥታ ሥርጭት ጀመረች፡፡ በሽያጩ ከአንድ ሳሙና የሚገኘው ትርፍ 57 ፔሶ ኮሚሽን ነው፤ 0.93 ዶላር አካባቢ ማለት ነው። ሽያጩን ከጀመረች ከስድስት ወራት በኋላ፣ እስከ ኅዳር ወር ድረስ ከ6 ሺሕ በላይ ሳሙናዎችን በመሸጥ ሙሉውን 350 ሺሕ ፔሶ ማሰባሰብ ቻለች፡፡
የሳሙናው ሽያጭ ባለፈው ዓመት በብድርና በአንድ የገቢ ምንጭ ውስጥ ስትላተም የቆየችውን የዶክተር ፋጢማ አልዛህራ ዲቲን ሕይወት ሌላ አቅጣጫ አስያዘው፡፡ ሕልሟ ተሳክቶ የ61 ዓመት እድሜ ያላቸው እናት ሚምቡንግ የዛሬ ሣምንት ረቡዕ ከአምስቱ የእስልምና መሠረቶች አንዱን ለመፈጸም ከሚሰበሰቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናን ጋር ለመቀላቀል ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ በረዋል፡፡ ይህ ፍጹም ደስታ ውስጥ የከተታት ዲቲ፤ “ለራሴ ቃል የገባሁት እርሷን ለመንከባከብ ነው፤ አሁንም እያደረግኩ ያለሁት ያንኑ ነው። ከልቤ የምፈልገው ብቸኛው ነገር ለእናቴ ምቹ ሕይወት መስጠት ነው” በማለት ተናግራለች፡፡ አክላም “ለማንኛውም ምዕመን ሐጅ ማከናወን ትልቅ ሕልም ነው፤ ሳሙና መሸጥ በመጨረሻ ወደ ሐጅ ያደርሰኛል ብዬ ፈጽሞ አልገመትኩም ነበር፤ ግን ሆነ” ብላለች፡፡ በመጨረሻ ለታመኑላት የቲክቶክ ተከታዮች ምሥጋና ማቅረብ አልዘነጋችም፤ በሒደቱ “ሐሳብህ ቅን እና መልካም ሲሆን ሰዎች በጉዞህ ሁሉ ከልብ እንደሚደግፉህም ተረድቻለሁ” ብላለች፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












