Homeዜናና ወቅታዊዜናበሠፋሪዎች ወረራ እና የ‘ባንዲራ ሠልፍ’ ብለው በሚጠሩት ትዕይነት ምክንያት መስጂደል አቅሷ ለሙስሊሞች...

በሠፋሪዎች ወረራ እና የ‘ባንዲራ ሠልፍ’ ብለው በሚጠሩት ትዕይነት ምክንያት መስጂደል አቅሷ ለሙስሊሞች ዝግ ተደረገ

በቁድስ ከተማ የእስራኤል ባለሥልጣናት ‘ኦልድ ሲቲ’ ሲሉ በሚጠሩት የ“ባንዲራ ሠልፍ” ትዕይንት ዋዜማ፣ ፍልስጤማውያን ሙስሊሞች ወደ መስጅደል አቅሷ እንዳይገቡ ታግደዋል፡፡ የእስራኤል ኃይሎች “የሠልፉንና የወረራውን ሒደት ለማመቻቸት ሲሉ” በወረራ ስር በምትገኘው የምሥራቅ ቁድስ ከተማ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥለዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ የፍልስጤማውያን መደብሮች እንዲዘጉ ተገደዋል፤ ነዋሪዎችም በቤታቸው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተላልፎባቸዋል፡፡

ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ የእንቅስቃሴ ገደቡ የተጣለው ንጋት ላይ ከፈጅር ሰላት በኋላ ነው፡፡ የእስራኤል ኃይሎች ወደ ሥፍራው ለመጠጋት የሚሞክሩ ምዕመናንን በመፈተሽ መታወቂያ ሲነጥቁ ታይተዋል፡፡ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በታች የሆኑ ወንዶች እና ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች ወደ መስጂዱ እንዳይገቡ ከልክለዋል።

በመቀጠልም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጽንፈኛ እስራኤላውያን በፖሊስ ታጅበው ቅዱሱ ሥፍራ ላይ ወረራ ፈጽመዋል፡፡ በጧቱ ክፍለ ጊዜ ብቻ ቢያንስ 800 እስራኤላውያን ወደ ሥፍራው የገቡ ሲሆን፣ ቀሪ ቡድኖችም ተከትለው ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በወረራው ወቅት አንዳንድ ሰዎች በመስጂዱ ቅጽር ውስጥ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችንና ጸሎት በማከናወን እስራኤልን ይወክላል የሚሉትን ሰንደቅ ሰቅለዋል።

በእስራኤል ባለሥልጣናት የ‘ባንዲራ ሠልፍ’ በመባል የሚጠራው ትዕይንት፤ እ.ኤ.አ. በ1967ቱ የስድስት ቀን ጦርነት ወቅት ምሥራቅ ቁድስን በቁጥጥር ስር አውለናል የሚሉበትን ዕለት ለማክበር የሚያደርጉት ነው። የእስራኤል ሰዎች ይህን ዕለት “ከተማዋ ዳግም የተዋሐደችበት” ብለው ይጠሩታል።

የዘንድሮው ትዕይንት ሐሙስ ፀሐይ ስትጠልቅ ጀምሮ ነገ ጁመዐ ምሽት ላይ ያበቃል፡፡ ይህ ቀን በዚህ ዓመት ፍልስጤማውያን በየዓመቱ ከሚያከብሩት የጥፋት ቀን (የውመል ነክባ) ጋር ገጥሟል፡፡ የነክባ ቀን እ.ኤ.አ. በ1948 የእስራኤል መንግሥት በሚመሠረትበት ወቅት በጽዮናዊያን ሚሊሻዎች አማካኝነት ከ750 ሺሕ በላይ ፍልስጤማውያን የተፈጸመባቸውን የዘር ማጥፋት ማስታወሻ ነው።

በቁድስ የሚገኘው የተከበረው ቅዱስ ሥፍራ (ሐረም አሽሸሪፍ) የእስልምና ሦስተኛው ቅዱስ ሥፍራ የሆነውን መስጂድ አል አቅሷንና በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የተገነባውን የአለት ጉልላት የያዘ ነው። ይህ ጉልላት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ሰማይ ያረጉበት ሥፍራ ነው ተብሎ ይታመናል። ከ1967 ጀምሮ ዮርዳኖስ እና እስራኤል በቅጽር ግቢው ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን የኢስላማዊ ወቅፍ እንዲያስተዳድርና እስራኤል ደግሞ የውጭ ደህንነትን እንድትቆጣጠር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። ሙስሊም ያልሆኑ አካላት በጉብኝት ሰዓታት ወደ ሥፍራው እንዲገቡ ቢፈቀድላቸውም፣ በውስጡ እንዲጸልዩ ግን አይፈቀድላቸውም። ጸሎት የተፈቀደው ለሙስሊሞች ብቻ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular