የአሜሪካ እስልምና ግንኙነት ምክር ቤት፤ “በአሜሪካ ሙስሊሞች ላይ የሚሰነዘረው ጥላቻ ሙሉ ለሙሉ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል” ያለው በካሊፎርኒያ በሚገኝ አንድ መስጂድ ላይ ጥቃት ተሰንዝሮ የሰዎች ሕይወት መቀጠፉን ተከትሎ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከጥቃቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ “በነገሩ እጅግ አዝነናል፤ ነገር ግን በጭራሽ አልተገረምንም። [ምክንያቱም] በአሜሪካውያን ሙስሊሞች ላይ የሚሰነዘረው ጥላቻ ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል” ብሏል።
የሙስሊሞች መብቶች ተሟጋች ቡድኑ አክሎም፤ በርካታ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ “ሙስሊሞች መጥፋት እንዳለባቸው”፣ “የአሜሪካ መስጂዶችና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መዘጋት እንደሚኖርባቸው”ና “ሙስሊሞች ከሀገራችን መባረር አለባቸው” ሲሉ መሰንበታቸውን አስታውሷል፡፡ ባለፈው ሣምንት ብቻ የምክር ቤት እንደራሴ ሪፐብሊካኖች በአሜሪካውያን ሙስሊሞች፣ በጸሎት ሥፍራዎቻቸው እና በሙስሊም ተማሪዎች ላይ ጥላቻን የሚያቀጣጥሉ የኮንግረስ ችሎት አካሄደዋል ብሏል፡፡ ድርጅቱ ለዚህ አስረጂ ብሎ የጠቀሰው ከ60 በላይ ሕግ አውጪዎችን በአባልነት የያዘውና በካፒቶል ሂል የሚገኘውን የሪፐብሊካኖች “ከሸሪዐ ነጻ ኮከስ” ነው፡፡
የዚህ ኮከስ አባላት “የእስልምና ሕግ በአሜሪካ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሥርዐት ውስጥ ሰርጎ እየገባ ነው” የሚል ሥጋት ያቀርባሉ፡፡ በዚህ መነሻ “የአሜሪካን ሕገ መንግሥትና ባሕላዊ እሴቶችን ከእስልምና ሕግ ተጽእኖ መጠበቅ አለብን” የሚሉ ናቸው፡፡ በዚህ በተለይ የሚታወቁት የትራምፕ አጋሩ የፍሎሪዳ ኮንግረስ አባል ራንዲ ፋይን ናቸው፡፡
የአሜሪካ እስልምና ግንኙነት ምክር ቤት በዚህ ሣምንት በካሊፎርኒያ ሳን ዲዬጎ በሚገኘው እስላማዊ ማዕከል ላይ የተፈጸመው ጥቃት “ሊገመት የሚችል ቢሆንም በጭራሽ ተቀባይነት የሌለው” መሆኑን በመጥቀስ ድርጊቱን ኮንኗል፡፡
ከአሜሪካ እስልምና ግንኙነት ምክር ቤት በተጨማሪ ሙስሊም ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቴ የተሰኘ የሙስሊሞች ተቋርቋሪ ቡድን፤ ጥቃቱ “በራሱ ጊዜ የመጣ ድንገተኛ ክስተት እንዳልሆነ በመጥቀስ፤ ባለፉት ዐሥር ዐመታት በእስልምና ላይ የሚሰነዘሩ ጥላቻዎችና ጥቃቶች 11 እጥፍ መጨመራቸውን ጠቅሷል፡፡ በተለይ ለዓመታት በበይነ መረብ የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሙስሊም ግለሰቦች፣ እንደ ‘ስቶፕ አንቲሰሚቲዝም’ ያሉ የመገናኛ መድረኮች “ሙስሊሞችን እንደ ሀገራዊ ሥጋት አድርገው የሚስሉ የሴራ ትንታኔዎችን ሲያናፍሱ” መቆየታቸውን ገልጿል፡፡
ከዴሞክራቶች ጋር የሚወግነው ጄ ስትሪት የተባለ የመብቶች ተሟጋች ቡድን ደግሞ በኤክስ ገጽ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ “የእስልምና ጥላቻን በግልጽ፣ በአስቸኳይ እና ያለምንም ማመንታት መጋፈጥ ይኖርብናል” ብሏል።
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ሳንዲዬጎ በሚገኘው የእስልምና ማዕከል ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት፤ የጸጥታ ሠራተኛን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመበት ማዕከል በስሩ መስጂድ እና ትምህርት ቤትን ያቀፈ ነው፡፡ የሳንዲዬጎ ፖሊስ አዛዥ ስኮት ዋል እንደተናገሩት፤ ጥቃቱን ፈጸመዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ከሟቾች መካከል ተገኝተዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












