Homeዜናና ወቅታዊዜናበኢትዮጵያ የወለድ አልባ ባንክ ዘርፍ አቅምን ለማሳደግ ያለመ አዲስ የልማት ፕሮግራም ይፋ...

በኢትዮጵያ የወለድ አልባ ባንክ ዘርፍ አቅምን ለማሳደግ ያለመ አዲስ የልማት ፕሮግራም ይፋ ተደረገ

በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የወለድ አልባ የባንክ እና የፋይናንስ ዘርፍ ይበልጥ ለማጠናከር እና የባለሞያዎችን አቅም ለመገንባት ያለመ አዲስ የበይነ መረብ የሞያ ማበልጸጊያ ፕሮግራም ይፋ ተደርጓል። ፕሮግራሙ ይፋ የተደረገው ዋና መቀመጫው በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በሚገኘው አልሁዳ የኢስላሚክ ባንክ እና ኢኮኖሚክስ ማዕከል ነው።

ማዕከሉ ይህን ያስታወቀው በዚህ ሣምንት የመርሐ ግብሩን ይፋ መደረግ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ ነው፡፡ በመግለጫው ላይ በሠፈረው መሠረት፤ ሥልጠናው ለሁለት ወራት የሚቆይ ነው፡፡ ከሰኔ 3 እስከ ነሐሴ 4/2018 ይሰጣል የተባለው የአቅም ግንባታ ሥልጠና፤ በኢትዮጵያ ሞያዊ አቅምን ለማጠናከር እና ከወለድ ነፃ የሆኑ የፋይናንስ ሥርዓቶችን ለማገዝ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።

ይህ የሥልጠና እና የልማት ፕሮግራም የሚከናወነው በኢትዮጵያ ባሉ አራት የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተዋናዮች ድጋፍ ነው፡፡ እነዚህም ድጋፍ ሰጪ አካላት የኢትዮጵያ የባንኮች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የወለድ ነጻ ፋይናንስ ባለሞያዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ መድኅን ሰጪዎች ማኅበር እና የኢትዮጵያ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበር ናቸው።

የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሐመድ ዙበይር ሙጋል እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ከወለድ ነፃ ፋይናንስ እጅግ ተስፋ ሰጪ እና ተለዋዋጭ ገበያዎችን ትወክላለች። በኢትዮጵያ የቁጥጥር ሥርዓት፣ ወጣት የሰው ኃይል እንዲሁም ጠንካራ የሥነ ምግባር የፋይናንስ አገልግሎቶች ፍላጎት እያደገ መምጣቱንም ጠቅሰዋል። “ከወለድ ነፃ ባንክ የፋይናንስ አማራጭ ብቻ ሳይሆን የፋይናንስ አካታችነት፣ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት እና ዘላቂ ልማትን የሚያበረታታ የተሟላ ሥርዓት ነው” ሲሉም ገልጸውታል።

በበይነ መረብ በነጻ የሚሰጠው የሥልጠና እና የልማት ፕሮግራሙ ላይ የባንክ ባለሞያዎች እና የፋይናንስ ተቋማት አመራሮች፣ የተቆጣጣሪ አካላት እና የፖሊሲ አውጪዎች፣ የተካፉል ኢንሹራንስ እና የማይክሮ ፋይናንስ ባለሞያዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን አሠራሮች፣ የሸሪዓ መርሆዎችን የጠበቁ የሐብት ማሰባሰቢያ እና የብድር አማራጮችን እንዲሁም የሥጋት መከላከያ ስልቶችን በተግባር የተደገፈ እውቀት እንዲጨብጡ የሚያስችል እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተቀማጭ ገንዘብ ከግማሽ ትሪሊዮን በማለፍ ከ520 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ የኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ ባለሞያዎች ማኅበር ባለፈው ወር አስታውቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular