Homeዜናና ወቅታዊዜና“የሸሪዓ ሕጉን መሠረት ያደረጉ ስምምነቶችን” የመዳኘት ሥልጣን የሚሰጠው የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች...

“የሸሪዓ ሕጉን መሠረት ያደረጉ ስምምነቶችን” የመዳኘት ሥልጣን የሚሰጠው የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅ በፓርላማ ጸደቀ

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 18/2018 ባካሄደው አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የተሻሻለውን የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል፡፡ አዋጁ ተጠሪነቱ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሆነ “የፌደራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች አስተዳደር ጉባዔ” እንዲቋቋም የሚፈቅድ ነው፡፡

ምክር ቤቱ ረቂቁን ያጸደቀው ከሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ከመረመረ በኋላ ነው፡፡ አዲሱ አዋጅ በ1992 “የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን አቋም ለማጠናከር” በሚል የጸደቀውን  የሚሽር ነው፡፡ በተሻረው አዋጅ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጋር “የወል ዳኝነት” የሚኖራቸው በውስን ጉዳዮች ላይ ነበር፡፡ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች እንዲመለከቱት በአዋጁ የተቀመጠው “የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የቀለብ አወሳሰን፣ አካለ መጠን ያልደረሱ ሕጻናት ሞግዚትነት፣ የወቅፍ፣ የሥጦታ ወይም የኑዛዜ ጉዳዮች”ን ነበር፡፡

የተሻሻለው አዋጅ በተመሳሳይ ለሸሪዓ ፍርድ ቤቶች በሸሪዓ ሕጉ ላይ የተመሠረቱ “የጋብቻና የጋብቻ ውጤት፣ የፍቺና የፍቺ ውጤት፣ የቀለብ አወሳሰን፣ አካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት አስተዳደግና ሞግዚትነት ወይም በቤተሰብ ተዛምዶና የሕግ ችሎታ ያጡ ሰዎች ላይ የሚነሱ ጉዳዮች”ን እንዲሁም “የወቅፍና የወቅፍ አስተዳደር (ናዚርነት)፣ የሥጦታ (ሂባ)፣ የውርስ፣ ውርስ ማጣራትና ውርስ ሐብት ክፍፍል ወይም የኑዛዜ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጉዳዮች”ን እንዲዳኙ “የወል ሥልጣን” ይሰጣል፡፡

አዲሱ አዋጅ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ጉዳዮችን ያካተተ ነው፡፡ በዚህም አግባብ ለሸሪዓ ፍርድ ቤት በግልጽ “የሸሪዓ ሕጉን መሠረት አድርገው የተመሠረቱ ስምምነቶችና ግንኙነቶችን” የመዳኘት ሥልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ በኅዳር 2017 ለውይይት በቀረበው “የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የሕግ ማዕቀፍ፣ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይል አስተዳደርን ችግሮች በመለየት የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ በተዘጋጀ” ሠነድ ላይ እንደሠፈረው፤ “ሸሪዓን መሠረት ያደረገ ባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ የሙአለ ንዋይ ገበያ (ካፒታል ማርኬት) እና ሌሎች የሸሪዓን ሕግ መሠረት አድርገው የተመሠረቱ ስምምነቶችና ግንኙነቶች” ጋር በተያያዘ የሚነሱ አለመግባባቶችን” የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች እንዲዳኙ ምክረ ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡

አዲሱ አዋጅ በተጨማሪም “በውጪ ሀገር የሞቱ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲፈጸም የሚፈቀድንና የጋብቻ ሥነ ሥርዓትን የሚያከናውኑ የሸሪዓ አጋቢዎች ፍቃድ መስጠትን” አካቷል፡፡ ከፍቺ ጋር በተገናኘ “በመደበኛ ፍርድ ቤት የተሰጠ የፍቺ ውሳኔን መሠረት በማድረግ ኒካህ እንዲወርድ የሚቀርብ ጥያቄን” በተመለከተ የመዳኘት ሥልጣን ይሰጣል፡፡

የፌደራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች አስተዳደር ጉባዔ እንዲቋቋም የሚያደርገው አዋጁ፤ ይህ ጉባዔ ተጠሪነቱ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሆኖ የራሱ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም መሆኑን ደንግጓል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የፌደራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የፌደራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ ተወካይ፣ በፌደራል ሽሪዓ ፍርድ ቤቶች ዳኞች የጋራ ስብሰባ የሚወከል አንድ የዳኞች ተወካይ፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዑለማ ጉባዔ አባላት ውስጥ ሁለት ተወካይ፣ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሚወከል በዳኝነት ሥራ የረዥም ጊዜ ልምድ ያለው ሙስሊም የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ፣ በሞያዊ ብቃት፣ በስነ ምግባሩ የተመሰገነና ማህበራዊ ተቀባይነቱ ከፍ ያለ፣ ለሕግ የበላይነትና ለሸሪዓ ፍትሕ ሥርዓቱ እድገት ቁርጠኝነት ያለውና የጎላ አስተዋጽዖ ያበረከተ ወይም ለማበርከት ይችላል ተብሎ የሚገመት በጉባዔው የሚመረጥ አንድ ሰውን በአባልነት ያካትታል፡፡ ከጉባዔው አባላት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ሴቶች በተወካይነት እንደሚካተቱም ይደነግጋል፡፡

በኢትዮጵያ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች በመንግሥት ድጋፍ የተቋቋሙት በ1934 ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular