Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችበአማራ ክልል የኢማሞች ግድያ መበራከት አሳስቦናል - የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት

በአማራ ክልል የኢማሞች ግድያ መበራከት አሳስቦናል – የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት

በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን ዳንግላ ወረዳ የመስጂድ ኢማም በነበሩት ሸይኽ ሱፊያን አደም ላይ ግድያ እንደተፈጸመ፤ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እሑድ ሰኔ 21/2018 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በምክር ቤቱ መረጃ መሠረት፤ ኢማሙ ቅዳሜ ሰኔ 20/2018 የተገደሉት ዕድሜያቸውን ሙሉ በኖሩበት በዳንግላ ከተማ ቀበሌ 02 በሚገኘው ተውፊቅ መስጂድ፣ የተለመደውን የዒሻእ ሰላት በኢማምነት መርተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው በር በመቃረብ ላይ ሳሉ ነው።

ከ“ሚንበር ቲቪ” ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሙሐመድ ኢብራሂም እንደተናገሩት፣ ሸይኽ ሱፊያን አደም በአዊ ዞን የዑለማ ምክር ቤት ውስጥ በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩና ከየትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ጋር “ምንም ዐይነት ጠብ የሌላቸው ሰላማዊ ሰው” ነበሩ።

ዳንግላ ወረዳ የመስጂድ ኢማም በነበሩት ሸይኽ ሱፊያን አደም

ጥቃቱ የተፈጸመው “ምሽት የኢሻእ ሰላትን አሰግደው ወደ ቤታቸው ሊገቡ ሲሉ በታጣቂዎች በተከፈተባቸው ተኩስ” መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱን ተከትሎ የአካባቢው የጸጥታ አካላት ሕብረተሰቡን ማነጋገራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በስብሰባው ላይ የዞኑ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አመራሮችም ተሳታፊ ሆነዋል።

መንግሥት የችግሩን አስከፊነት በማመልከት ከኅብረተሰቡ ጋር መግባባት ላይ መድረሱን የገለጹት ሸይኽ ሙሐመድ፣ በአሁኑ ሰዓት የዞኑ መጅሊስ አመራሮች ጉዳዩን በቅርበት ለመከታተል በዳንግላ ከተማ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህ ጥቃት በክልሉ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችንና ቁርአን ቤቶችን ኢላማ ያደረገ የመጀመሪያው አለመሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ ጎልተው የወጡ ናቸው ብለው ከጠቀሷቸው ጥቃቶች መካከል በዳንግላ ወረዳ ከአንድ ወር በፊት አንድ ሙስሊም ባለሐብት ገንዘብ አምጣ በሚል አስገዳጅ ዛቻ መኖሪያ ቤቱ ድረስ በመዝለቅ በታጣቂዎች መገደሉ ይገኝበታል፡፡ በተጨማሪም በጎንደር ከተማ ባለፈው የረመዳን ወር አንድ የመስጅድ ኢማም ሲገደሉ፤ በከተማዋ የነበሩ ስድስት ሐሪማዎች ተበትነዋል። በመካነ ሰላም በተመሳሳይ ሁኔታ የመስጅድ ኢማሞችና ሙአዚኖች ተገድለዋል፡፡

ከ“ሚንበር ቲቪ” ጋር ቆይታ ያደረጉት ሌላኛው የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ተወካይ ሸይኽ ኢድሪስ ሑሴን በበኩላቸው፣ በአሁኑ ሰዓት ዋነኛው ትኩረት የኢማሙን ሞት የማጣራት ሥራ መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ወደፊት የሟችን ቤተሰብ የመደገፍ ሥራ ሊሠራ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ሸይኽ ሱፍያን አደም ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነበሩ፡፡

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሙሐመድ ኢብራሂም፤ አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ለኢማሞቹ ጥበቃ እንዲያደርግና የመንግሥት የጸጥታ አካላትም የሃይማኖት አባቶችን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር አስፈላጊውን ሥራ ሁሉ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት አስተዳደር እና የጸጥታ መዋቅር እስካሁን ድረስ ስለ ኢማሙ ግድያ ያለው ነገር የለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular