Homeዜናና ወቅታዊዜናካንሠር በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀን 26 ሺሕ ሰዎችን ይገድላል - የዓለም ጤና...

ካንሠር በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀን 26 ሺሕ ሰዎችን ይገድላል – የዓለም ጤና ድርጅት

የዓለም ጤና ድርጅት አዲስ ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው፤ ካንሠር በዓለም ዙርያ የሰው ልጅ ላይ አስከፊ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያደረሰ ይገኛል፡፡ በየዓመቱ በአማካይ 20 ነጥብ 6 ሚሊዮን አዳዲስ ሕሙማን የሚመዘገቡትና ወደ ዐሥር ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ለኅልፈት የሚዳረጉበት ካንሠር፤ ከልብና የደም ዝውውር ሥርዐት በሽታዎች (Cardiovascular disease) በመቀጠል በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለተኛው ዋነኛ የሞት መንስኤ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በሽታው በቀን ከ26 ሺሕ በላይ ሰዎችን እየቀጠፈ እንደሚገኝ በማመልከት በሐብታም እና ድኻ ሀገሮች መካከል ሊኖር የሚችለው ታክሞ የመዳን ምጣኔ መስፋቱንም ይፋ አድርጓል፡፡ የሳምባ ካንሠር በዓለም አቀፍ ደረጃ በካንሠር ምክንያት ለሚከሰት ሞት ዋነኛው መንስኤ ነው። የሳምባ፣ የፕሮስቴት እና የአንጀት ካንሠር በወንዶች ላይ ከሚታዩት በጣም የተለመዱ የካንሰር ዓይነቶች መካከል ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡ በሴቶች ላይ ደግሞ የጡት፣ የሳምባ እና የአንጀት ካንሠር ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚመዘገቡት የካንሠር ሕመሞች መካከል ከአሥሩ ወደ አራቱ ገደማ የሚሆኑት አስቀድሞ መከላከል ከሚቻሉ የአደጋ መንስኤዎች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በተለይም በንክኪ (በተለይም በግብረ-ሥጋ ግንኙነት) የሚተላለፈው ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ፣ ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ የተባሉት የጉበት በሽታዎች እንዲሁም የሆድ ዕቃ ባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች፤ ከአልኮል፣ ከትንባሆ፣ ከከፍተኛ የሰውነት ክብደት እና ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማነስ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው በሽታውን አስቀድሞ መከላከል የሚቻል ተብለው ተለይተዋል፡፡

በሪፖርቱ ላይ የተሳተፉ ባለሞያዎች እንደሚሉት፤ አንድ በካንሠር በሽታ የተያዘ ሰው የመዳን ዕድሉ በአብዛኛው የተመሠረተው በሚኖርበት አካባቢ የተመሠረተ ነው፡፡ በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ አራት ሰዎች መካከል አንዱ የመያዝ ዕድል ይኖረዋል ተብሎ ቢገመትም፤ በበሽታው የሚሞተው ግን ከ12 ሰዎች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች በሽታውን አስቀድሞ የመመርመርና የሕክምና አገልግሎት የማግኘት ዕድል ውስን በመሆኑ ምክንያት የሞቱ መጠን እጅግ የከፋ ነው፡፡

ሪፖርቱ በተለይም በጡት ካንሠር ሕይወትን የማዳን ሒደት ላይ ያለውን ግልጽ ልዩነት አጉልቶ አሳይቷል፡፡ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች በበሽታው ከተያዙ ሴቶች መካከል ወደ 90 በመቶው ገደማ የሚሆኑት ቢያንስ ለአምስት ዓመታት በሕይወት ይቆያሉ፡፡ አነስተኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ግን ይህ አኃዝ ወደ 40 በመቶ ዝቅ ይላል፡፡

ድርጅቱ የበሽታውን መከላከያ መንገዶች ለማሥፋት፣ ሕክምናውን ለማሻሻል እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በካንሠር እንክብካቤ ላይ ያለውን ልዩነት ለመቀነስ አፋጣኝ ርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር፤ በየዓመቱ የሚመዘገበው የሕሙማን ቁጥር እ.አ.አ በ2050 ወደ 35 ሚሊዮን ገደማ ሊደርስ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡ ይህ ቁጥር አሁን ካለው ወደ እጥፍ ገደማ ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም፤ “ካንሠር ሁላችንንም በቅርበት ሊነካ የሚችልና እጅግ ግላዊ በሽታ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው ከካንሠር የመዳን ዕድሉ በተወለደበት አካባቢ ወይም በሚያገኘው ገቢ ላይ መመርኮዝ የለበትም፤ በሪፖርቱ ላይ የተመዘገቡት ኢ-እኩልነቶችም ሊቀየሩ የማይችሉ አይደሉም፤ የተሳሳቱ ውሳኔዎች ውጤቶች በመሆናቸው፣ በጠንካራና በተቀናጀ ርምጃ ሊቀለበሱ ይችላሉ” ሲሉ ሁኔታው በትብብር ሊለወጥ የሚችል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular