Homeዜናና ወቅታዊዜናበኢትዮጵያ የወሊድ ምጣኔ መቀነሱን የሚያሳይ አዲስ ሪፖርት ይፋ ተደረገ

በኢትዮጵያ የወሊድ ምጣኔ መቀነሱን የሚያሳይ አዲስ ሪፖርት ይፋ ተደረገ

  • በአዲስ አበባ ከመላው ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የተባለው 2.3 ልጅ አማካይ የወሊድ ምጣኔ ተመዝግቧል

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከነሐሴ 2016 እስከ ሚያዝያ 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ የሰበሰበውን መረጃ መሠረት በማድረግ 5ኛውን የኢትዮጵያ የሕዝብ እና ጤና ቅኝት ማጠቃለያ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ጥናቱ በኢትዮጵያ የወሊድ ምጣኔ መቀነሱን ያሳያል፡፡

በጥናቱ ላይ ከ21 ሺሕ በላይ ሴቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ የሀገሪቱ ወቅታዊ የሕዝብ ስብጥር፣ የጤና እና የኑሮ ሁኔታ የሚያሳይ ሰፊ መረጃ ተካቶበታል።

የአገልግሎቱ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ የአንዲት ሴት አማካይ የወሊድ ምጣኔ በ1992 ከነበረበት 5.5 ልጆች በአሁኑ ወቅት ወደ 4 ልጆች ዝቅ ብሏል። በክልሎች መካከል የወሊድ ምጣኔው ልዩነት የተመመዘገበበት ሲሆን፣ ከፍተኛው የወሊድ ምጣኔ በሱማሌ ክልል (6.5 ልጆች) ተመዝግቧል፡፡ ዝቅተኛው ደግሞ በአዲስ አበባ (2.3 ልጆች) ሆኖ ተመዝግቧል።

በሪፖርቱ መሠረት ይህ የወሊድ ምጣኔ ከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ያላቸው ሴቶች ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ካላቸው ሴቶች ጋር ሲነፃፀሩ የመውለድ እድላቸው በአጠቃላይ ይቀንሳል። እንዲሁም የቤተሰብ ሀብት እየጨመረ ሲሄድ የወሊድ ምጣኔው ሲቀንስ፣ በተቃራኒው በድኻ ቤተሰቦች ውስጥ ያሉ ሴቶች ብዙ ልጆችን ይወልዳሉ፡፡

ከሕፃናት ሞት ጋር በተገናኘም ከ1992 ጀምሮ ከ1 ሺህ በሕይወት የተወለዱ ሕፃናት ከ97 ሞት ወደ 39 ቀንሷል፡፡ ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሞት በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከ166 ወደ 51 ሞት ቀንሷል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ቤተሰቦች በአማካይ 4.4 አባላት ሲኖራቸው፣ 28 በመቶ የሚሆኑትን የኢትዮጵያ ቤተሰቦችን ሴቶች ያስተዳድራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የቤተሰብ አባላት 42 በመቶ የሚሆኑት ከ15 ዓመት በታች ናቸው።

ሌላው ሪፖርቱ ያካተተው ጉዳይ የመሠረተ ልማት እና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ 57 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ያገኛል። ይሁን እንጂ 71 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በመኖሪያ ግቢው ውስጥ የውሃ መስመር የለውም።

መሠረታዊ የሽንት ቤት አገልግሎት የሚያገኘው ሕዝብ 31 በመቶ ብቻ እንደሆነ ያሳየው ሪፖርቱ፤ 27 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ አሁንም በሜዳ ላይ የመጸዳዳት ልማድ አለው ብሏል።

የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ 64 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የሚያገኝ ቢሆንም ለምግብ ማብሰያነት ዘመናዊና ንፁህ የኃይል አማራጮችን ወይም የኤሌክትሪክ ምድጃ፣ ጋዝ የመሰሉትን የሚጠቀመው 5 በመቶ ብቻ ነው።

በከተማ የኤሌክትሪክ ምጣድ አጠቃቀም 31 በመቶ ሲሆን በገጠር 2 በመቶ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ መኪና፣ የጭነት መኪና ወይም ሞተር ሳይክል/ስኩተር ያላቸው አራት በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች እንደሆኑም ሪፖርቱ አሳይቷል።

በሌላ በኩል የዓለም የሕዝብ ብዛት 8.2 ቢሊዮን በላይ መሻገሩን የዓለም ባንክ ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስታውቋል። የዩናይትድ ኔሽን ፖፑሌሽን ፈንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው ደግሞ፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት 135 ሚሊዮን በማለፍ ከዓለም 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በሕዝብ ብዛት ከዓለም ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘችው ሕንድ ስትሆን፤ ከ1. 41 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ብዛት ያላትን ቻይና አስከትላለች። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular