የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የተያዘው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት በይፋ ወደ ተግባር ተሸጋግሯል ሲል አሳውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደዘገበው፤ ከዚህ በፊት የተሠሩ ሥራዎችን እንደ መልካም ልምድ በመውሰድ በቀጣይ ዓመታት እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ሰፊ መርሐ ግብር ተቀርጾ በፋይናንስም ሆነ በሌሎች አቅሞች ረገድ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሙሐመድ ዓብዱራሕማን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎችን የቤት አቅርቦት ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስ የሚያግዝ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ይህ እቅድ የዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችን ዘላቂ ድጋፍ ያካተተ ነው ተብሏል፡፡
ከእነዚህ መካከል በተባበሩት መንግሥታት የሰፈራ ፕሮግራም (UN-Habitat) መንግሥት የጀመረውን ይህን ተነሳሽነት ለመደገፍ አራት የተለያዩ የፖሊሲ እና የቴክኒክ ፓኬጆችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የፕሮጀክቱ ሌላኛው ወሳኝ አጋዥ አካል ይሆናል የተባለው የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ነው። መንግሥት ምቹ አሠራሮችን መዘርጋቱ የግሉ ዘርፍ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ እና በኮንስትራክሽን ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፍ ሰፊ በር ከፍቷል ተብሏል።
መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት መዘጋጀቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ ያደረጉት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ነበር፡፡ አዲሱ የቤት ልማት ፖሊሲ ተቀርጾ በካቢኔ መጽደቁንና በሁሉም ክልሎች የተቀናጀ ንቅናቄ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ገለጸው ነበር፡፡ ግንባታው በመንግሥት በጀት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም የመንግሥትና የግል አጋርነት መዋቅሮችን በስፋት መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












