1/ ከሸሪዓ ሕግ ጋር የተጣጣመ የቤት ባለቤቶች ኢንሹራንስ ፕሮግራም በአሜሪካ ይፋ ተደረገ
በአሜሪካ የመጀመርያ ነው የተባለውና ከሸሪዓ ሕግ ጋር የተጣጣመ የቤት ባለቤቶች ኢንሹራንስ ፕሮግራም ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህ አገልግሎት ከእምነታቸው ጋር የሚጣጣም እና ከመደበኛው አገልግሎት የተለየ አማራጭ የሚፈልጉ ቤተሰቦችን ዒላማ ያደረገ ነው፡፡ ከሸሪዓ ሕግጋት ጋር የሚጣጣመውን ፕሮግራም “ተካፉል አሜሪካን” ይፋ ያስጀመረው የአልጎሪዝም ኢንሹራንስ አገልግሎቶች ሰጪው ጃጓር ሪስክ ነው፡፡ ኩባንያው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን፣ ዳታን እና የሒሳብ ቀመሮችን በመጠቀም የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን የሚቀርጽ፣ የሚያስተዳደር እና ለገበያ የሚያቀርብ ነው፡፡
2/ ኢንዶኔዥያ ዓለም አቀፍ ሱኩክ አወጣች
የኢንዶኔዥያ መንግሥት በሦስት፣ አምስት እና አስር ዓመት የመክፈያ ጊዜ የተከፋፈለ በጠቅላላው 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ዓለም አቀፍ ሱኩክ (እስላማዊ ቦንድ) አውጥቷል፡፡ በዝርዝሩ መሠረት የሦስት ዓመት ጊዜ ያለው የ500 ሚሊዮን ዶላር ሱኩክ የ5 ነጥብ 45 በመቶ ትርፍ ምጣኔ፣ የአምስት ዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር በ5 ነጥብ 85 በመቶ ትርፍ ምጣኔ እንዲሁም የአስር ዓመት ጊዜ ያለው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በ6 ነጥብ 25 የትርፍ ምጣኔ አቅርቧል፡፡ ይህ ሱኩክ ከቀረበው መጠን በ2 ነጥ 9 እጥፍ ብልጫ ያለው የባለሐብቶች ፍላጎት (Oversubscription) አግኝቷል፡፡ ይህ የሱኩክ ሽያጭ በቦኤፍኤ ሴኩሪቲስ፣ ዱባይ ኢስላሚክ ባንክ፣ ኤች.ኤስ.ቢ.ሲ፣ ጄፒ ሞርጋን እና ኬ.ኤፍ.ኤች ካፒታል አስተባባሪነት የተከናወነ ነው፡፡ የሀገሪቱ መንግስት በተናጠል ስምንት የሸሪዓ ተኮር ሰነዶችን በጨረታ በማቅረብ 16 ነጥብ 65 ትሪሊዮን የኢንዶኔዥያ ሩፒያ (921 ነጥብ 62 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር) ማሰባሰብ ችሏል፡፡
3/ ግብጽ የሕዝብ እዳን ለመቀነስ በቀይ ባሕር አካባቢ የሚገኝ ሰፊ መሬት ከሱኩክ ዋስትና ባለፈ ለእዳ ማካካሻ እንዲውል አዲስ የአዋጅ ማሻሻያ አጸደቀች፡፡ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዓብዱልፈታህ አል ሲሲ፤ የሕዝብን እዳን ለመቀነስ እና የመንግሥት ሱኩክ ለማውጣት እንዲውል አዋጅ ያጸደቀችው በቀይ ባሕር ግዛት የሚገኝ መሬትን ነው፡፡ ለገንዘብ ሚኒስቴር በተላለፈው በዚህ መሬት ባለሐብቶች ገንዘብ ሲያበድሩ የባለቤትነት ድርሻ ስለሞኖራቸው ከንብረቱ ከሚገኘው ገቢ ተካፋይ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
4/ የሳዑዲው የሪል እስቴት ቴክኖሎጂ ኩባንያ ከአሜሪካ የግል ብድር አቅራቢ ጋር ያለውን የሙራባሃ የፋይናንስ አቅርቦት አሳደገ
የሳዑዲው የሪል እስቴት ቴክኖሎጂ እና ፊንቴክ ኩባንያ ኢጃሪ መቀመጫውን በአሜሪካ ካደረገው የግል የብድር አቅራቢ ‘ፓርትነርስ ፎር ግሮውዝ’ ጋር ያለውን የሙራባሃ የፋይናንስ አቅርቦት ወደ 50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አሳድጓል።
ኢጃሪ የፋይናንስ አቅርቦቱን ያሳደገው እ.አ.አ በ2024 በተመሠረተው የፋይናንስ ግንኙነት ላይ ተመስርቶ ነው። ይህም የቤት አከራዮች ዓመታዊ የኪራይ ክፍያቸውን በቅድሚያ እንዲቀበሉ እና ተከራዮች ደግሞ መጠኑን በየወሩ ከፋፍለው እንዲከፍሉ ለሚያስችለው የኢጃሪ «አሁን ተከራይተው በኋላ ይክፈሉ» መድረክ ግብይቶች የተለየ የገንዘብ ድጋፍ ያቀርባል።
ኢጃሪ በአሁኑ ወቅት በ40 የሳዑዲ ከተሞች ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማካተት የፋይናንስ ሞዴሉን ወደ ንግድ ቤቶች ኪራይ ለማስፋት አቅዷል። የፋይናንስ አቅርቦት እድገቱ ኢጃሪ በመኖሪያ ቤት ኪራይ ዘርፍ ያለውን ቀጣይ የዕድገት ምዕራፍ እና ወደ ንግድ ቤት ኪራይ የሚያደርገውን ጉዞ እንደሚደግፍ የኢጃሪ ተባባሪ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የዚድ አል-ሸምሲ ተናግረዋል።
በሳዑዲ ዓመታዊ የኪራይ ግብይት መጠን ከ60 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሚሆን የተገመተ ሲሆን በነሐሴ ወር 2018 የኪራይ ግብይቶች ጠቅላላ ዋጋ በ32 በመቶ አድጎ 10.62 ቢሊዮን የሳዑዲ ሪያል ደርሷል። ኢጃሪ እስካሁን ድረስ ከ500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የኪራይ ክፍያዎችን ለማመቻቸት ጥያቄዎችን እንደተቀበለ አስታውቋል። (ሚንበር ቲቪ)












