Homeዜናና ወቅታዊዜናገበያ እንዴት ዋለ?

ገበያ እንዴት ዋለ?

1/ 12ኛው የአፍሪካ እስላማዊ ፋይናንስ ሽልማት በሞሪሸስ ሊካሄድ ነው

የአልሁዳ እስላማዊ ባንክ እና ኢኮኖሚክስ ማዕከል 12ኛውን የአፍሪካ እስላማዊ ፋይናንስ ሽልማት ኅዳር 22/2019 በሞሪሸስ እንደሚያካሂድ ይፋ አድርጓል። ለ12ኛው ጊዜ የሚካሄደው የዕውቅና መድረክ በአፍሪካ አህጉር ከወለድ ነጻ የእስላማዊ ባንክና ፋይናንስ ዘርፍ ለማሳደግ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተቋማትን፣ ባለሙያዎችን እና ውጤታማ አዳዲስ አሠራሮችን ለመሸለም የሚዘጋጅ ነው።

ሽልማቱ ኅዳር 22 ከሚካሄደው 12ኛው የአፍሪካ እስላማዊ ፋይናንስ ጉባኤ ጎን ለጎን የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማትን ከተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት፣ ባለሀብቶች፣ የሸሪዓ ምሁራንና ከዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋር የሚያገናኝ መድረክ እንደሆነ ተገልጿል።

2/ የፓኪስታን የግል ዘርፍ የባንክ ብድር በከፍተኛ ደረጃ አደገ

በፓኪስታን ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠው የተጣራ የባንክ ብድር በከፍተኛ ደረጃ ሲያድግ መደበኛው ባንኮች በቅርንጫፍ በኩል የሚሰጡት የኢስላማዊ ባንክ አገልግሎት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል።  

በፓኪስታን ከሐምሌ 2018 እስከ ጥቅምት 2019 ባሉት አራት ወራት ውስጥ ባንኮች ለግሉ ዘርፍ ያቀረቡት የተጣራ ብድር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ3,717 በመቶ በመጨመር 782.44 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን የፓኪስታን ስቴት ባንክ አስታውቋል።

ከጠቅላላው የተጣራ ብድር ውስጥ ትልቁን ድርሻ የያዘው በመደበኛው ባንኮች ስር የሚተዳደሩት የኢስላማዊ የባንክ ቅርንጫፎች ሲሆኑ ወደ 555.75 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ የብድር ፋይናንስ አቅርበዋል። በተቃራኒው ሙሉ በሙሉ በእስላማዊ የባንክ አሰራር የሚመሩ ባንኮች ደግሞ 27.41 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን የተጣራ የብድር ተመላሽ ማድረጋቸው ተገልጿል።

3/ ባንግላዴሽ ለገጠር መሠረተ ልማት ግንባታ የሚውል የ30 ቢሊዮን ታካ የአጭር ጊዜ ሱኩክ ለጨረታ ልታቀርብ ነው

የባንግላዴሽ ማዕከላዊ ባንክ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የገጠር መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል 30 ቢሊዮን የባንግላዴሽ ታካ ወይም 240.66 ሚሊዮን ገደማ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያለው የመንግሥት የኢንቨስትመንት ሱኩክ ኅዳር 22/2019 በጨረታ ሊያቀርብ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ባንግላዴሽ በሀገሪቱ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የምታወጣው የአጭር ጊዜ የመንግስት ሱኩክ ሰነዱ በሸሪዓ ሕግ መሰሠረት በኪራይ ስምምነት ወይም ሱኩክ ኢጃራ በሚባለው ኢስላማዊ የፋይናንስ ሞዴል ላይ የተመሠረተ ነው። ባለሐብቶች ዓመታዊ 7.5 በመቶ ትርፍ ያገኙበታል ተብሏል፡፡ በተያያዘ የባንግላዴሽ ማዕከላዊ ባንክ የ10.81 ቢሊዮን ታካ እስላማዊ የገንዘብ አቅርቦት አመቻችቷል።

የባንግላዴሽ ማዕከላዊ ባንክ ኅዳር 1/2019 ባቀረበው የሰባት ቀናት እስላማዊ የገንዘብ አቅርቦት ጨረታ 10.81 ቢሊዮን የባንግላዴሽ ታካ ወይም 85.9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አቅርቦ ሙሉ በሙሉ በባንኮች መወሰዱን አስታውቋል።

4/ ኢራን የመንግሥት ሙራባሃ ሰነዶችን ለመሸጥ የመጀመርያ ሻጮችን ለመምረጥ ጨረታ አወጣች

የኢራን የኢኮኖሚና የፋይናንስ ጉዳዮች ሚኒስቴር 23 በመቶ ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔ ላላቸው የመንግሥት የሙራባሃ እስላማዊ የፋይናንስ ሰነዶች የመጀመርያ ሻጭ ሆነው የሚያገለግሉ ብቁ ባንኮችንና የፋይናንስ ተቋማትን ኅዳር 6፤ 2019 የጨረታ ሰነዳቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።

የመንግሥት ሰነዶቹ በቅናሽ ዋጋ የሚቀርቡ ሲሆን ቀዳሚ ሻጭ ለመሆን የሚወዳደሩ ተቋማት እስከ አራት ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 200 ትሪሊዮን የኢራን ሪያል ወይም 104.9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያላቸውን ሰነዶች ለመግዛት ቃል መግባት ይጠበቅባቸዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular