እሑድ , ذو الحجة 17, 1445
Google search engine
Homeዜናና ወቅታዊዜናመጅሊስ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቅረቡ ታወቀ

መጅሊስ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቅረቡ ታወቀ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ለምክክር ሒደት የሚቀርቡ የሀገሪቱን ሙስሊሞች አጀንዳዎች ለምክክር ኮሚሽን ማቅረቡ ታወቀ። መጅሊስ ካቀረባቸው ዘጠኝ አጀንዳዎች ውስጥ “ታሪክና ትርክት” እንዲሁም “ሀገራዊ እና ሕዝባዊ ምልክቶች” በድጋሚ እንዲቃኙ የሚጠይቀው ይገኝበታል።

ምክር ቤቱ አጀንዳዎቹን ያካተተበትን ሰነድ ማቅረቡን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ትናንት ሰኞ ግንቦት 19/2016 በዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አረጋግጧል። ሚንበር ቲቪ ከመጅሊስ ባገኘው መረጃ የቀረበው ሰነድ ባለ ሃያ ገጽ ነው።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያቀረበውና ሚንበር ቲቪ የተመለከተው ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ በአጀንዳነት የቀረቡት ዘጠኝ ጉዳዮች ናቸው።

እነዚህም ታሪክና ትርክት፣ ሀገራዊና ሕዝባዊ ምልክቶች፣ የሲቪል መብቶችና ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል፣ የሕዳጣን (Minority) መብት፣ የኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባል መሆን፣ የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት፣ ለሙስሊም ጠልነት ዕውቅና መስጠት እና ማስተካከል፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንዲሁም አካታች ኢኮኖሚና ፋይናንስ ማስፈን የሚሉት ናቸው።

መጅሊስ በቀዳሚነት ባስቀመጠው ታሪክና ትርክት ውስጥ የታሪክ፣ የሀገርና የሀገር አንድነት ጅማሬን፣ የሃይማኖት እና ሕዝቦችን አመጣጥ ትርክትን መከለስ አስፈላጊ መሆኑን ጠይቋል። የማኅበረ ኢኮኖሚ ታሪክ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ የሙስሊሞችን ታሪክ ያካተተ ማድረግ የሚለውም ይገኝበታል።

የኢትዮጵያን ታሪክ የሙስሊሞችን ታሪክ ያካተተ ማድረግ በሚለው ሥር የኢትዮጵያ ታሪክ የሚል ርእስ የያዙ ሀገር አቀፍ ታሪኮች የሙስሊሙን ታሪክ “በተለጣፊና ተጨማሪነት ወይም በጎንዮሽና በተቀናቃኝ” አድርጎ በመሳል እንደሚቀርቡ ያብራራል።

በታሪክና የሃይማኖት ጭቆናዎች ሆነው ሳሉ በብሔር ጭቆና ተደርገው የቀረቡትን ዳግም መከለስ እንዲሁም በታሪክ ፍሰት የጊዜ አከፋፈሎች ሙስሊም አካታች በሆነ መንገድ መቃኘት እንደሚኖርባቸው የተጠየቀውም በዚህ ክፍል ነው።

ምክር ቤቱ ባቀረበው ሰነድ ሀገራዊና ሕዝባዊ ምልክቶችን በተመለከተ የዘረዘረው በሁለተኛው አጀንዳ ነው። በዚህ ክፍል ሀገራዊ ጀግኖችን፣ ሀገራዊ የታሪክ ክስተቶችንና ቦታዎችን፣ የመንገድ አሠያየም፣ ሕዝባዊ ሥፍራዎችና መጠሪያዎች የተመለከቱ ጉዳዮች ተጠቅሰዋል። ሰነዱ ሕዝባዊ ሥፍራዎችና መጠሪያዎች አካላትና “የአንድ ወገን ሃይማኖታዊ መገለጫዎች መሆን” እንዳልነበረባቸው በመግለጽ ይህ መስተካከል የሚኖርበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁሟል።

በተመሳሳይ ሙዝየሞችና የታሪክ ሥፍራዎች፣ ብሔራዊ መዝሙር፣ የሀገር ወካይ ምልክቶች፣ ሰንደቅ አላማ፣ ሚዲያና ሥነ ጥበብ እንዲሁም የመማሪያ መጽሐፍት ላይ ሙስሊም ውክልና ማግኘት እንደሚኖርበትም መጅሊስ በሰነዱ አስፍሯል። ሰነዱ በቀሪ ሰባት አጀንዳዎችም ላይ በተመሳሳይ ማብራሪያዎችን አስቀምጧል።

በኢትዮጵያ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ውይይት ለማካሄድ በሒደት ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በታኅሣሥ 2014 በጸደቀ የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች፣ በመንግሥት እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮችን እንደሚለይ አሥፍሯል።

ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡለትን እነዚህን አጀንዳዎች ካደራጀ በኋላ ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የመለየት ሚና በአዋጁ ተሰጥቶታል። ተወካይ ያስመርጣሉ ተብለው ከተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን እና የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የተገለሉ ኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ዕድሮች እና የንግዱ ማኅበረሰብ ተካተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ

ሆኖም በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት መካተት አለባቸው ያለው መጅሊስ፣ የሙስሊሙ ውክልናም በቁጥሩ ልክ መሆኑ አለበት በሚል የተወካይ ልየታ በድጋሚ መቃኘት እንዳለበት ቅሬታውን ከዚህ ቀደም በደብዳቤ ማቅረቡን አስታውቆ ነበር።

የምክክር ኮሚሽን እንዳለው ከሆነ በ10 ክልሎችን እና የከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ አጠናቋል። ኮሚሽኑ ልየታ ያላካሄደባቸው የአማራ እና ትግራይ ክልሎች ናቸው። ምክክር ኮሚሽኑ ልየታ ባጠናቀቀባቸው አካባቢዎች ወደ ምክክር ምዕራፍ ሊሸጋገር መሆኑንም ትናንት በነበረው መግለጫው አስታውቋል። የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የምክክር ምዕራፍ ነገ ረቡዕ ግንቦት 21/2016 በአዲስ አበባ እንደሚጀመር ተገልጿል።

ለሰባት ቀናት በሚቆየው በዚህ ምክክር ላይ የሚገኙ ተሳታፊዎች በምክክርና በውይይት የአጀንዳ ሐሳቦችን ያቀርባሉ ተብሏል። ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ያዘጋጀው ይህ የምክክር ምዕራፍ ከ2 ሺሕ 500 በላይ ተወካዮችን ተሳታፊ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments