Homeዜናና ወቅታዊዜናለ12ኛ ክፍል ፈተና ላፕቶፕ እንዲያዘጋጁ በመታዘዙ ጫና ውስጥ መግባታቸውን ወላጆች ተናገሩ

ለ12ኛ ክፍል ፈተና ላፕቶፕ እንዲያዘጋጁ በመታዘዙ ጫና ውስጥ መግባታቸውን ወላጆች ተናገሩ


የትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በበይነ መረብ ለመስጠት እቅድ በያዘለት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና፣ በግል ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች ልጆቻቸው የመፈተኛ ላፕቶፕ እንዲያዘጋጁ በመታዘዙ ጫና ውስጥ መግባታቸውን ተናገሩ፡፡

ሚኒስቴሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው አሠራር በመንግሥትም ሆነ በግል ትምህርት ቤት የሚማሩ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞችን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲፈተኑ ቢያደረግም፣ በተያዘው ዓመት ከመደበኛው አሠራር በተጨማሪ ተማሪዎችን በተመረጡ አካባቢዎች በበይነ መረብ ለመፈተን እቅድ ይዟል፡፡ ለዚህ እንዲያግዝም ትምህርት ቤቶች ላፕቶፕ እንዲያዘጋጁ ትዕዛዝ መተላለፉንም የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሆኖም “በቂ የሆነ የላፕቶፕ አቅርቦት የለንም’ ያሉ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ተፈታኞች በራሳቸው እንዲያሟሉ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡ “ሚንበር ቲቪ” ያናገራቸው የተማሪዎች ወላጆች ይህ ውሳኔ ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደከተታቸው ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የመንግሥትም ሆነ የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ለማስፈተን የመፈተኛ ላፕቶፖችን እና ከኔትዎርክ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ግብዓቶች ማሟላት እንደሚገባቸው ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ገልጧል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ያስተላለፈው ትዕዛዝ በራሳቸው በትምህርት ቤቶቹም ላይ ጫና ማሳረፉን ሚንበር ቲቪ ከትምህርት ቤቶች አስተዳደር ሠራተኞች ሰምቷል፡፡

አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ለመፈተኛ የሚውለውን የግል ላፕቶፕ ባለባቸው የአቅም ውስንነት ሙሉ ሉሙሉ ማቅረብ ባለመቻላቸው፣ ተማሪዎቹ በግል ላፕቶፕ ይዘው እንዲመጡ ማዘዛቸውን በተለያየ አካባቢ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤት አስተዳደር እና ርእሰ መምህራን ለሚንበር ቲቪ ገልጸዋል፡፡

ከትምህርት ቤቶቹ ውስጥ በዘንድሮው ዓመት 115 ተማሪዎችን ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎችን የሚያስቀምጠው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የአወሊያ ትምህርት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰዒድ አስማረ፣ ለፈተና የሚያስፈልገው ላፕቶፕ ትምህርት ቤቱም ሆነ ተማሪዎቹ ላይ ጫና ማሳደሩን ለሚንበር ቲቪ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ትምህርት ቤቱ ጫናውን ለመጋራት ተማሪዎች ላፕቶፑን በራሳቸው እንዲያሟሉ ትዕዛዝ ቢተላለፍም ትምህርት ቤቱ በተለይ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎችን የሚጠበቅበትን ለማሟላት ጥረቱን መቀጠሉን ጠቁመዋል። ሥራ አስኪያጁ ትምህርት ቤቱ የሚያደርገው ጥረት ሊሳካ የሚችል መሆኑን ርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ሐረገወይን ገረሱ በርካታ ትምህርት ቤቶች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባዘዘው መሠረት ዝግጅት እያደረጉ ቢሆንም አገልግሎቱ የመጀመሪያ በመሆኑ በፈተና ወቅት የኢንተርኔት መቆራረጥና ተመሣሣይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ያላቸውን ሥጋት ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ትዕዛዙን ካስተላፈው የትምህርት ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በተመረጡ 25 አካባቢዎች በበይነ መረብ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በወረቀት ከሐምሌ 3 እስከ 11/2016 ፈተናውን እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ የማኅበራዊ ሣይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ከሐምሌ 3 እስከ ሐምሌ 5/2016 ለፈተና የሚቀመጡ ሲሆን የተፈጥሮ ሣይንስ ተማሪዎች ደግሞ ከሐምሌ 9 እስከ ሐምሌ 11/2016 ይወስዳሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)


RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular