በደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ የምትገኘው ታይላንድ፣ የሐላል ኢንዱስትሪ ማዕከል ይፋ አደረገች፡፡ ሀገሪቱ በአዲሱ ማዕከል በሐላል ምርቶች እና ኤክስፖርት ቀጠናውን የመምራት ዓላማ ይዛለች ተብሏል፡፡
የማዕከሉን መከፈት ይፋ ያደረጉት የሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ፒምፓትራ ዊቻኩል፣ ታይላንድ የሐላል ኢንስዱስትሪ ማዕከሉን ይፋ ከማድረግ ጎን ለጎን የሐላል ሥራ ፈጣሪዎችን አቅም ማጎልበት ላይ እንደምትሠራ ገልጸዋል፡፡
የታይላንድ ሐላል ኢንዱስትሪ ማዕከል የተቋቋመው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስሬታ ታቪሲን ብሔራዊ የሐላል ኢንዱስትሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ነው፡፡ “ታይ ኢንዱስትሪ ሴንተር” የተሰኘው ማዕከል 21 የሐላል ኤጀንሲዎችን ያካተተ ነው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የበላይ ጠባቂነት የተቋቋመው የታይላንድ የሐላል ኢንዱስትሪ ማዕከል፣ ፖሊሲ እና የዘርፉን የልማት ዕቅዶች የመንደፍ ኃላፊነት ተሰጥታል፡፡
በፍጥነት እያደገ መሆኑ የሚነገርለት ዓለም አቀፉ የሐላል ገበያ፣ 2.3 ትሪሊዮን ዶላር ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ሲሆን እ.አ.አ በ2025 2.5 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ከሐላል ገበያ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የምግብ እና መጠጥ ዘርፍ ነው፡፡ 64 በመቶ ድርሻ ያለው የምግብ እና መጠጥ ዘርፍ፣ 1.4 ትሪሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡
በኢትዮጵያ በሐላል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለምርቶች የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐላል ሠርተፍኬት እንደሚሰጥ ይናገራል፡፡ የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በተመሳሳይ ከእርድ ጋር በተገናኘ ለበርካታ ዓመታት እውቅና ሲሰጥ ቆይቷል።
በግሉ ዘርፍ ላለፉት አራት ዓመታት እውቅና እየሰጠ የሚገኘው “ኢትሴፍ” የተሰኘ ድርጅት ሲሆን፣ በነሐሴ 2014 በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሐላል ምግብና ቱሪዝም አውደ ርዕይና ጉባዔ አዘጋጅቶ ነበር። ኢትሴፍ ከሥጋ እና የሥጋ ምርቶች ጋር በተገናኘ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ዕውቅና የተሰጠው የመጀመርያ ድርጅት መሆኑን በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












