በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚንቀሳቀሰው ሳፋሪኮም፤ ከገልፍካፕ ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር በመተባበር ከሸሪዓ ጋር ተስማሚ አዲስ የገንዘብ ገበያ ፈንድ ይፋ ማድረጉን አስታውቋል። “ዚዲ ሸሪዓ” የተሰኘው አዲሱ አገልግሎት በተለይም ሙስሊም ደንበኞች በእስልምና መርህ ላይ የተመሠረተ ኢንቨስትመንት ላይ መሳተፍ እንዲችሉ የፋይናንስ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
ኩባንያው እንዳሳወቀው ከሆነ፣ አዲሱ የገንዘብ ገበያ ፈንድ ሙሉ በሙሉ በሸሪዓ ሕግጋት የታቀፉ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ገንዘብ ሊቀየሩ የሚችሉ ሕጋዊ የባንክ ኢንቨስትመንቶች ላይ ብቻ ያተኩራል። ይህም ከማንኛውም ዓይነት ከወለድ ነጻ ትርፍ ለማስገኘት የሚያስችል ነው፡፡
በኬንያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድና ቁጥጥር የሚደረግበት ፈንዱ፤ በገልፍካፕ ኢንቨስትመንት ባንክ የሸሪዓ አማካሪ ቦርድ የሚመራ ነው፡፡
የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር ንዴግዋ፤ የፋይናንስ ተሳትፎን ማሳደግ ማለት አገልግሎቶቻችንን ከደንበኞች የተለያየ ፍላጎትና እሴቶች ጋር ማጣጣም ማለት መሆኑን በመጥቀስ፤ በ’ዚዲ ሸሪዓ’ በኩል “ኢንቨስትመንትን ቀላል፣ ተመጣጣኝ እና ተደራሽ በመሆን ደንበኞች ከሚመሩበት የሕይወት እሴት ጋር የተጣጣመ አማራጭ አቅርበናል” ብለዋል።
የገፍካፕ ኢንቨስትመንት ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳዑድ ሸህባል በበኩላቸው፤ በኤም ፔሳ ዲጂታል መድረክ ላይ የተገነባው አዲሱ የገንዘብ ገበያ ፈንድ፣ ሙስሊሞችና የሞራል ደንብን የሚጠብቅ ኢንቨስትመንትን የሚመርጡ አካላት ሐብታቸውን እምነታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲያሳድጉ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል” ሲሉ ገልጸዋል።
ደንበኞች በ100 የኬንያ ሽልንግ መነሻ ገንዘብ አገልግሎቱን መጀመር የሚችሉ ሲሆን፣ ከፍተኛው የገንዘብ መጠን ገደብ አልተቀመጠለትም። ይሁን እንጂ በኤም ፔሳ መደበኛ የዕለት የኢንቨስትመንት ገደብ እስከ 500 ሺህ የኬንያ ሽልንግ መገበያየት እንደሚቻል በመግለጫው ተካቷል። (ሚንበር ቲቪ)












