ግብጻዊቷ የበረራ አስተናጋጅ አዛ ረምዚ በሠርጓ ዋዜማ የየመኑ ሑውሲ (አንሳሩላህ) ታጣቂ ቡድን ቅዳሜ እለት በሳዑዲ ዐረቢያ ንጉሥ ኻሊድ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት ሕይወታቸው ከተቀጠፉት 12 ሰዎች መካከል ሆናለች፡፡
የ28 ዓመት ዕድሜ የነበራት አዛ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ በትውልድ ቦታዋ በሚደረገው የሠርግ ሥነ ሥርዐት ላይ ለመታደም ለመልስ ጉዞ በዝግጅት ላይ እንደነበረች ተዘግቧል፡፡
የሳዑዲ ዐረቢያው ፍላይ ናስ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ፤ ሕይወቷ ሊያልፍ የቻለው በጥቃቱ ወቅት በአየር መንገዱ ውስጥ በሥራ ላይ በነበረችበት በደረሰባት ጽኑ የመቁሰል አደጋ ምክንያት ነው፡፡ ይህ ክስተት በትውልድ ቦታዋ የግብጿ ሄራ ግዛት በምትገኘው የመሐመዲያ አካባቢ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ሐዘን ፈጥሯል፡፡
ሳዑዲ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ በግብጽ የሚገኙ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ተጠቃሚዎች በወጣቷ የበረራ አስተናጋጅ የሚላኩ የሐዘን መግለጫዎች የተሞሉ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎችም ከሕይወቷ ትላልቁ አጋጣሚዎች አንዱ በሆነው የሠርግ ሥነ ሥርዐቷ ዋዜማ ሕይወቷ መቀጨቱን በማሰብ ሐዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
የሳዑዲ ዐረቢያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እንደገለጸው፤ በንጉሥ ኻሊድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቅዳሜ እለት በተፈጸመው በዚህ ጥቃት አዛ ረምዚን ጨምሮ 12 ሰዎች ሲሞቱ፣ 309 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡
በታጣቂ ቡድኑ በተሰነዘረው ጥቃት የተገደሉት 4 የሳዑዲ ዐረቢያ፣ 2 የባንግላዴሽ፣ 1 አንድ የአሜሪካ፣ 1 የግብጽ፣ 1 የዮርዳኖስ፣ 1 አንድ የሶሪያ፣ 1 የፍልስጤም እና 1 የሱዳን ዜጎች ናቸው። ቡድኑ በተመሳሳይ እሑድ እለት በሰነዘረው ጥቃት 1 ሰው ሲገደል፣ 11 ሰዎች ቆስለዋል ተብሏል፡፡
የሑውሲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህይያ ሰሪ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ ሁሉም የመርከብ ድርጅቶች፣ የአየር መገድ ኩባንያዎች፣ ሠራተኞች እና ተጓዦች በሳዑዲ ዐረቢያ የሚገኙ አየረ መንገዶችን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል፡፡ አክለውም “ከመካ እና መዲና በስተቀር፣ የሀገሪቱ አየር መንገዶች እና የአየር ክልል ለጥቃት የተጋለጡ የውጊያ ቀጣና ናቸው” ብለዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












