ኢትዮጵያ ለ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን 12 ሺሕ ኢትዮጵያውንን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ልካለች፡፡ የመጨረሻዎቹ ሑጃጆች ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሰኔ 1/2016 በረራ አከናውነዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኃላፊች የመጨረሻዎቹን ሑጃጆች ከመላካቸው አስቀድሞ በሰጡት መግለጫ፣ ከምዝገባ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ለሑጃጆች የተደረገውን መሰናዶ አብራርተዋል፡፡
በማብራሪያው ላይ ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ከሑጃጆች የጤና አገልግሎት ጋር የተገናኘው ተጠቃሽ ነው፡፡ ኃላፊዎቹ እንዳሉት በዘንድሮው ዓመት ኢትዮጵያውን ሑጃጆች የጤና እክል ቢገጥማቸው የሕክምና እገዛ ለማድረግ ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች ተዘጋጅተዋል፡፡
የክሊኒኮቹ ብዛት ሦስት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እነዚህ ተንቀሳቃሽ ክኒሊኮች ሑጃጆች የጤና እክል ሲገጥማቸው ባሉበት ደርሰው የሕክምና እገዛ ይሰጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኃላፊዎች ባለፈው ዓመት በተመሣሣይ ለሑጃጆች የሕክምና እገዛ የሚሰጥ ክሊኒክ በማዘጋጀት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ለሑጃጆቹ ለተዘጋጀው ተንቀሳቃሽ ክሊኒክ የመድኃኒት አቅርቦት የተደረገው በኦማን መንግሥት መሆኑን የምክር ቤቱ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ በተዘጋጁ ክሊኒኮቹ ውስጥ ከዚህ መድኃኒት ውስጥ የአገልግሎት ጊዜ ያልጠናቀቀው ተመርጦ እንደሚቀርብ የተገለጸ ሲሆን፣ ቀሪው መድኃኒት በምክር ቤቱ እንዲገዛ መደረጉም በማብራሪያው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ካዘጋጀው ውጪ ሑጃጆቹን የምታስተናግደው ሳዑዲ ዐረቢያ ለሐጅ ሥነ ሥርዐቱ ተሳታፊ ምዕመናን አገልግሎት የሚሰጡ 5 ሺሕ ዶክተሮች ዝግጁ መሆናቸውን ትናንት ሰኞ አስታውቃለች፡፡ ሀገሪቱ ዶክተሮቹን ጨምሮ የተሳካ የሕክምና እገዛ ለመስጠት 183 የጤና አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ማቋቋሟን ያስታወቀችው ሳዑዲ፣ ዶክተሮቹን ጨምሮ 32 ሺሕ ሰዎች ለአገልግሎቱ መሰናዷቸውን አጠናቀዋል ብላለች፡፡ እነዚህ የጤና ጣቢያዎች እና ባለሞያዎች በመካ እና መዲና ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ሳዑዲ ዐረቢያ እስካሁን ድረስ 1.3 ሚሊዮን በላይ ምዕመናንን ከመላው ዓለም ተቀብላለች፡፡ በ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












