Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችሜሱት ኦዚል፣ የኡዉጉር ሙስሊሞች እና ኤርዶጋን

ሜሱት ኦዚል፣ የኡዉጉር ሙስሊሞች እና ኤርዶጋን

በዓለም እግር ኳስ ሜሱት ኦዚል የተከበረ ሥም ነው፡፡ ምትሐተኛ እግሮች የታደለው ኦዚል፤ በአውሮፓ እግር ኳስ የላቀ ተሰጥኦ ካላቸው ተጫዋቾች ከፊት ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ በአሕጉሩ የእግር ኳስ መድረክ የታፈረ ሥም ባለው ሪያል ማድሪድ እንዲሁም ለእንግሊዙ አርሰናል መጫወት ችሏል፡፡ በተወለደበት ጀርመን ለሻልከ 04 እና ወርደር ብሬመን ተጫውቶም አሳልፏል፡፡ የዓለም ዋንጫን ጨምሮ በርካታ ድሎችን አሳክቷል፡፡ የዘር ግንዱ የሚመዘዘው ከቱርክ ቢሆንም በብሔራዊ ቡድን የወከለው ጀርመንን ነው፡፡ አያቱ ከቱርክ ወደ ጀርመን ተሰደው የልጆቻቸው ኑሮ በዚያው እንዲመሠረት ማድረጋቸው ለጀርመን ለመጫወቱ ሰበብ ሆኗል፡፡

ሜሱት ኦዚል በመጨረሻ የእግር ኳስ ዘመኑን ያሳለፈው የዘር ግንዱ በሚመዘዝበት ቱርክ ለፌነርባቼ በመጫወት ነው፡፡ እ.አ.አ በ2023 እግር ኳስ በፕሮፌሽናል መድረክ መጫወት በቃኝ ካለ ሁለት ዓመታት በኋላ አዲስ መልኩን በዚህ ሣምንት ለዓለም ገልጧል፡፡ የቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች ከዚህ በኋላ ፖለቲካን መቀላቀሉን ይፋ አድርጓል፡፡ የፖለቲካ መድረኩን የተቀላቀለው የሰርጉ አድማቂ በነበሩት የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን በሚመሩት ኤኬ ፓርቲ (Adalet ve Kalkınma Partisi) በኩል ነው፡፡ ይህ የኦዚል ውሳኔ በእግር ኳሱ ዓለም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

በርግጥ ኦዚል የፖለቲካውን ዓለም በይፋ ከመቀላቀሉ በፊትም ቢሆን በፍላጎትም ይሁን አለፍላጎቱ ከፖለቲካ እና ከፖለቲከኞች ጋር የሚላተምበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ አንደኛው አጋጣሚ የተፈጠረው በቻይና ስለሚገኙት ስለኡዉጉር ሙስሊሞች በመናገሩ ነው፡፡

አንዱን ቀን በኢንስታግራም ገጹ፡- ‘በምሥራቅ ቱርክስታን (ኡዉጉሪስታን)፤ ሙስሊሞችን ከሃይማኖታቸው ለመነጠል ግፍ እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ አሳዳጆቻቸው ቁርኣን ያቃጥላሉ፤ መስጂድ እና ትምሕርት ቤታቸውን ዘግተውም አላበቁም፤ ኢማሞችን ገድለው፣ ወንዶችን አፍሰው በማጎሪያዎች በመቆለፍም አላበቁም፤ ሴቶቹን ወስደው ለቻይኖች በግዳጅ ድረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲፈጸም ሙስሊሞች ጉዳዩን በዝምታ እየተመለከቱ ነው፡፡ ዝም ማለታቸው ለሚፈጸመው ግፍ ይሁንታ እንደመስጠት እንደሚቆጠር አያውቁምን?’ አለ፡፡

ከዚህ በኋላ የቻይና ፖለቲከኞች ተቆጡ፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ሲቆጡ የሚጫወትበት አርሰናል ኦዚልን አኮረፈው፡፡ በድረ ገጹ ‘አርሰናል ከፖለቲካ ገለልተኛ ነው፤ የሜሱት ንግግር እኛን አይወክልም’ የሚል ጻፈ፡፡ መልዕክቱ ለቻይኖች እንዲደርስ ዌቦ በተሰኘው የሀገሪቱ ዝነኛ መተግበሪያ ላይ ሰፈረ፡፡ ክለቡ ይህን ሲጽፍ ቻይኖቹ ኦዚልን ይጎዳል ያሉትን ሁሉ አደረጉ፡፡ ፕሮ ኢቮሉሽን ሶከር የተሰኘው ቪድዮ ጌም ተጫዋቹን ‘አስወጣ’፡፡ የሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ሲሲቲቪ አርሰናል ከማንችስተር ሲቲ ጋር ያደጉትን ቀጣይ ግጥሚያ በቻይና እንዳይታይ አገደ፡፡ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ‘ኦዚል ከመናገሩ በፊት የመረጃዎቹን እውነተኛነት ማጣራት አለበት፤ በሐሰት መረጃ ተታሏል’ ሲሉ የሀገራቸው መንግሥት በሙስሊሞች ላይ የሚፈጽመውን ለማስተባባል ሞከሩ፡፡

ኦዚል የኡዉጉያህ ሙስሊሞች ግፍ እየተፈጸመባቸው ነው ብሎ መናገሩ ውሎ አድሮ ነገር የሚመዝ ሆኖ ተከትሎት፤ ከአንድ ዓመት በኋላ አሰልጣኙ ከቡድኑ ስብስብ ውጭ አደረገው፡፡ አሰልጣኙ ሚኬል አርቴታ ውሳኔውን ያሳለፍኩት ‘እግር ኳሳዊ በሆነ ምክንያት ነው’ ቢልም ሙሉ ለሙሉ ያመነው አልነበረም፡፡ በርካቶች ከውሳኔው ጀርባ ፖለቲካ አለበት ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ አርቴታ ‘ለውሳኔዬ መነሻ የሆነኝ ሜሱት በልምምድ ሜዳ አመርቂ ብቃት አለማሳየቱ ነው’ ነበር ያለው፡፡ ከዚህ ውዝግብ በኋላ ጥቂት ቆይቶ ወደ ቱርክ ያመራው ኦዚል፤ በመጨረሻ ፖለቲካን በይፋ በመቀላቀል ከሚዜው ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ጎን ተቀምጧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular