ለ25 ዓመታት የቆየውን የበሻር አል አሰድ አገዛዝ ካሰናበተች 10 ሳምንታት ያስቆጠረችው ሶሪያ፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት በተለያዩ ዓለማት ከተበተነው ሕዝቧ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ወደ ሀገሯ ሲመለስ፤ አዲሱ መሪዋ አሕመድ አሸረዕ ደግሞ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡ የቀድሞው ሐያት ተህሪር አል ሻም የተሰኘው ታጣቂ ኃይል አዛዥ፤ ደማስቆን ተቆጣጥረው ጥቂት ከቆዩ በኋላ የፕሬዝዳንት ሹመታቸው ይፋ ሲደረግ ሳዑዲ ዐረቢያ እና ቱርክን መጎብኘት ችለው ነበር፡፡
ጉብኝቱ ቀጥሎ ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ ካይሮ ሊበሩ ቀጠሮ መያዛቸውን የሀገሪቱ ዜና አገልግሎት ባወጣው መረጃ አረጋግጧል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ወደ ካይሮ የሚያመሩት በግብጽ አቻቸው ዐብዱልፈታህ አል ሲሲ ግብዣ ነው፡፡ የአል ሲሲ ግብጽ የካቲት 25/2017 ዐረብ ሊግ የጠራውን አስቸኳይ ጉባዔ ታስተናግዳለች፡፡ ጉባዔው የሚመክረው ስለ ጋዛ መሆኑን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይ የተጋበዙት አሕመድ አሸረዕ፤ ከግብጹ አል ሲሲ ጋር በሹመታቸው ማግሥት የ“እንኳን ደስ አለህ” መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ፊት ለፊት ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
መጪው የካይሮ ጉባዔ የተጠራው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛን ነዋሪዎች የማጽዳት ዕቅድ ይፋ አድርገው መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ ነው፡፡ ትራምፕ ጋዛን ለሪልእስቴት አመቺ ሥፍራ መሆኑን ጠቁመው፤ ነዋሪዎቹን በሌላ አካባቢ ስለማሥፈር ሲናገሩ ለሠፈራ የመረጡት ግብጽ እና ጆርዳንን እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሁለቱም ሀገራት ይህን ዕቅድ በመሪዎቻቸው ተቃውመውታል፡፡ ይሁን እንጂ ሀገራቱ ከአሜሪካ ከፍተኛ የሚባል ዓመታዊ የገንዘብ ድጋፍ ስለሚያገኙ ጫናውን በቀላሉ መቋቋም ሊቸግራቸው እንደሚችል ስለጉዳዩ የሚጽፉ ይናገራሉ፡፡
እንደ አልጀዚራ ዘገባ ከሆነ፤ ከዐረብ ሊግ ጉባዔ አስቀድሞ ባለፈው ሳምንት ጁመዓ የግብጽ እና ጆርዳን መሪዎችን ያካተተ ስብሰባ በሪያድ የተከናወነው በዚህ አግባብ ነው፡፡ “በወንድማማች ማዕቀፍ” የተካሄደ ነው በተባለው በዚህ ስብሰባ ላይ፤ እንግዶቹን ያስተናገደችው ሳዑዲ ዐረቢያ ልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን፣ የኳታሩ አሚር ተሚም ቢን ሐማድ፣ የግብጹ ዓብዱልፈታህ አልሲሲ፣ የጆርዳኑ ንጉሥ ዓብደላ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሙሐመድ ቢን ዛይድ አልነህያን፣ የኩዌት አሚር ሸይኽ መሻል አል አሕመድ እና የባሕሬን ልዑል ሰልማን ቢን ሐማድ ሰአል ኸሊፋ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ቀርቧል የተባለው በግብጽ የተዘጋጀ የትራምፕ “እቅድ ማርከሻ” አማራጭ ምክረ ሐሳብ ነው፡፡ የዐረብ ሀገራት በዚህ ይፋ ባልወጣ ምክረ ሐሳብ ላይ ከዐረብ ሊግ ጉባኤ በፊት ከስምምነት ላይ የሚደርሱ ከሆነ በጉባዔው ይፋ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ ለቴሌቪዥን ጣቢያው የተናገሩት የቀድሞ የግብጽ ረዳት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሑሴን ሀሪዲ፤ የሪያዱን ስብሰባ ለዐረብ ሀገራት እና ለፍልስጤማዊያን “አንገብጋቢ” ነው ብለውታል፡፡ የቀድሞው የግብጽ ባለሥልጣን የስብሰባውን አንገብጋቢነት ያስረዱት የትራምፕን አቅድ አደገኛነት በማስታወስ ነው፡፡
ለሑሴን ሀሪዲ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዕቅድ በጋዛ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የፍልስጤማዊያንን እና የዐረቡን ዓለም የሰባት ዐስርት ዓመታት ትግል “ገደል የሚከት” ነው፡፡ ለዚህም የዊሊያም ሼክስፒርን አገላለጽ ተውሰው ለዐረብ ሀገራት ቀጣዩ ጊዜ ቁርጠኛ “መሆን ወይም አለመሆናቸውን” የሚያሳዩበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለሀገራቱ እና ለፍልስጤም በዚህ መሃል የተቀመጠ ሦስተኛ አማራጭ የለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












