የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ ከቀናት በኋላ በሚጀምረው የረመዳን ወር ሀገር አቀፍ የቁርኣን ውድድር ሊያካሔድ መሆኑን አስታወቀ። መጋቢት 7/2017 (ረመዳን 17) ይካሔዳል የተባለው ውድድር ሥፍራ አዲስ አበባ ከተማ አብዮት አደባባይ እንደሚሆን ገልጿል።
ምክር ቤቱ ይህን የገለጸው ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 15/2017 በጽሕፈቱ ቤቱ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። «ቁርኣን የእውቀት እና የሰላም ምንጭ» በሚል መሪ ቃል ይካሔዳል በተባለው ውድድር ላይ፣ ክልሎች ተሳታፊ እንደሚልኩ ተገልጿል።
ውድድሩ ቁርኣን ሰማያዊ ብቻ ሳይሆን ምድራዊ ክብርና ክፍታን የሚያጎናፅፍ የዕውቀትና የሰላም ምንጭ መሆኑን ለማሳየት፣ በሀገሪቱ የሚገኙ የቁርኣን ተማሪዎች እንዲሁም መድረሳዎች እንዲነቃቁ ለማስቻል እንዲሁም ቁርኣን በእውቀት የዳበረ፣ በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ በማፍራት ረገድ ከፍ ያለ ሚና እንዳለው ለማሳወቅ እንዲሁም የቤተሰብ መሠረትና መድረሳ በመሆን የማኅበረሰብ ገንቢ የሆኑት ሴቶች ከቁርኣን ጋር ያላቸው ትስስር ጎልቶ የሚታዩበት መሆኑን ለመግለጽ በሚል ዓላማ የሚደረግ ነው ተብሏል።
በውድድሩ በሁለቱም ፆታ አንደኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የመኪና ሽልማት ይበረከታል የተባለ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ለሚያጠናቅቅ ወንድ ተወዳዳሪ የሐጅ ዕድል እንዲሁም ለሴት ተወዳዳሪ ብር አምስት መቶ ሺሕ ይበረከታል ተብሏል።
ሦስተኛ ደረጃ የሚወጡ ወንድም ሴትም ተወዳዳሪዎች ለእያንዳዳቸው ብር ሦስት መቶ ሺሕ እንደሚበረከትም በዛሬው መግለጫ ላይ ተነግሯል። ስለ ውድድሩ የተናገሩት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ በዕለቱ በሚከናወነው የቁርኣን ውድድር ላይ ኅብረተሰቡ እንዲታደም ጥሪ በማቅረብ የኢፍጣር ዝግጅትም በዚያው የመርሐ ግብረ አካል እንደሚሆን ጠቁመዋል። (ሚንበር ቲቪ)












